“ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ የሰላም በር ለሁሉም ተከፍቷል” ለገሱ ቱሉ (ዶ.ር)

84

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ባለፉት ሥድስት ዓመታት የነበሩ የለውጥ ጉዞዎች፣ የሰላም፣ የደኅንነት እና የበጋ ልማት ሥራዎችን በተመለከተ አንስተዋል፡፡

የሰላም እና የደኅንነት መረጋገጥ ለሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች እውን መኾን እና ለአንዲት ሀገር እድገት መሠረቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የተረጋጋ እና የሰከነ ሥርዓት ከየትኛውም ወገን የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመቋቋም፣ ለመመከት፣ ተግዳሮቶቹን ለመሻገር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ማኅበረሰብን ለማዘመን ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ያልተረጋጋ አካባቢ ለማኅበራዊ ደኅንነት እና እድገት ፈታኝ መኾኑንም ገልጸዋል ዶክተር ለገሰ፡፡

ሰላም እና መረጋጋትን ማረጋገጥ ለልማት ትኩረት ለማድረግ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ሰላማዊ ማኅበረሰቦች ለዘላቂ ልማት አስፈላጊ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ የራሷን ልማት ለማፋጠን እና ብልጽግናዋን ከማረጋገጥ በላይ በቀጣናው፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከፍ እንዲል ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ለገሰ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት እና ትብብር በማጎልበት ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን እድትጠብቅ ይረዳታል ብለዋል፡፡ ማኅበረሰባዊ መግባባት መፍጠር፣ አብሮነትን ማሳደግ፣ የጋራ ግንኙነቶችን እና እሴቶችን ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ አካታችነትን እና ተሳትፎን ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ያለፉ ቁርሾዎችን በትዕግሥት እና በይቅርታ መፍታት እና ስብራቶችን መጠገን ያስፈልጋል ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡ የለውጡ መንግሥት ሥር የሰደዱ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮችን ከሥራቸው ለመንቀል የተረጋጋ አዎንታዊ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር አልሞ እየሠራ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ የለውጡ መንግሥት ሁሉን ወገኖችን የሚያሳትፍ እና የሚያግባባ፣ የሚያስተሳስር፣ አብሮነትን በትብብር የሚያጎለብት፣ ብዝኃነትን እና አንድነትን የሚያሳልጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በብሔራዊ ትርክት ላይ የተመሠረተ ሀገረ መንግሥት እየገነባ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ያለፉ ስብራቶችን እና ቁርሾዎችን የሚጠግን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለመተግበር እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ልዩነቶችን እና ያላግባቡ ጉዳዮችን በውይይት እና በምክክር፣ በሰጥቶ መቀበል እና በድርድር ለመፍታት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተሳትፎን እና አካታችነትን ለማጎልበት በርካታ እርምጃዎች መውሰዳቸውንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ገለልተኛ ተቋማትን እንድትገነባ መሠረት መጣሉንም ገልጸዋል፡፡ ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ የሰላም በር ለሁሉም ተከፍቷል ብለዋል፡፡ የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የይቅርታ እና የምሕረት እሳቤ በተጨባጭ እንዲተገበር ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ያጠበቡ አሳሪ ሕጎች እንዲሻሻሉ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ለአካታች፣ ኅበረ ብሔራዊ፣ ፌዴራላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት ጥሏል ብለዋል፡፡ ወርኃ መጋቢት የኢትዮጵያ የመበልጸግ እና የመለውጥ ፍላጎት እውን የኾነበት ብቻ ሳይኾን ሁልንተናዊ ብልጽግና እና መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ የተጣለበት ነው ብለውታል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብትን ከውድቀት እና ከስብራት የሚያወጡ ለውጦች የተካሄዱበት እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከችግር ወጥተው ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በግብርናው ዘርፍ የተጀመረው ለውጥ ዓለም አቀፍ እውቅና ከማስገኘቱም በላይ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ስኬቶቹ የተመዘገቡት በፈተና ውስጥ አልፈው እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ተግዳሮቶቹ ተጨማሪ አቅም እና እድል ኾነው እንዲያገለግሉ ተደርገው በመመራታቸው ለስኬት አብቅተውናል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያን ማደግ የማይፈልጉ መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከመጋቢት እስከ መጋቢት ታሪካዊ አሻራ በማኖር አንድነትን፣ ማኅበራዊ ትስስርን በማጎልበት ብልጽግናዋን ከማረጋገጥ የሚያስቆማት እንደሌለ ማረጋገጥ እንወዳለን ብለዋል፡፡

ዶክተር ለገሰ ኅብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር ለሁላችንም የምትመች ሀገር ከመገንባት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን በመገንዘብ ለስኬታማነቱ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleየማኅበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር)