“በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

24

አዲስ አበባ: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደተቻለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ በቀጣይም 70 ሺህ የሚኾኑ ዜጎችን ለመመለስም ዝግጅት እየደረገ ነው ተብሏል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሦስት ወራት 50 ሺህ 327 ዜጎች ወደ ሀገር ቤት መመለስ ተችሏል፡፡

በመግለጫቸው 20 ሺህ 455 ስደተኞችን ከአፍሪካ ሀገራት ማለትም ከሱዳን፣ ከታንዛኒያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬኒያ፣ ከዝምባቡዌ እና ከናይጀሪያ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ስለመቻሉ ነው ያብራሩት፡፡ 21 ሺህ የሚኾኑት ከሳዑዲ አረቢያ እና ቀሪዎቹ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ማለትም ከኩዌት፣ ከኦማን፣ ከኳታር እና ከባህሬን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ስለመደረጉ ነው የገለጹት። ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ደግሞ ከእስራኤል እና ከጣሊያን መመለስ ስለመቻሉም አስገንዝበዋል።

መንግሥት ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት። በዚህም በዋናነት በሀገር ውስጥ የሥራ እድልን ማሳደግ እና ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪቶችን ማድረግ በቅድሚያ በትኩረት እየተሠራባቸው ነው ተብሏል። በቀጣይም 70 ሺህ የሚኾኑ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራ 16 ተቋማትን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ቦክስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤቱን ለመመክፈት ስምምነት አካሂዷል። ስምምነቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አካሂደዋል። በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ካደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲኾን በልማቱ አንዲሳተፉ መግባባት ስለመደረሱ ነው ቃል አቀባዩ ያስረዱት፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ያለውን የደም እጥረት ችግር ለመቅረፍ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች የደም ልገሳ አካሂደዋል።
Next article“ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡ የሰላም በር ለሁሉም ተከፍቷል” ለገሱ ቱሉ (ዶ.ር)