በአማራ ክልል ያለውን የደም እጥረት ችግር ለመቅረፍ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች የደም ልገሳ አካሂደዋል።

19

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደም እጦት የአንድም ሰው ህይዎት ማለፍ የለበትም በሚል ተነሳሽነት ነው የጠቅላይ መምሪያው አባላት ደም የለገሱት። በደም ልገሳው መርሐ ግብርሩ ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እንደተናገሩት ሠራዊቱ ደም መለገስን ባህሉ አድርጎታል፤ የሚታወቅበትን ሕዝባዊ ባህሪ ዛሬም በተግባር ያረጋግጣል ብለዋል።

ይህ የተልዕኳችን አንዱ አካል ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እኛ እንደ ሠራዊት “ደም በመለገስ ህይዎትን፤ በመስጠት ደግሞ ሀገር እናስቀጥላለን” ብለዋል። ሠራዊቱ የሚተካውን ደም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ኾኖ በመለገስ በደም እጦት ምክንያት ሊከተል የሚችለውን ሞት ይታደጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ለኢትዮጵያ ሰላም ቆስለው ሆስፒታል የሚገኙ እና ያገገሙ ቁስለኞችም ጭምር በደም ልገሳው ተሳትፈዋል ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ምክንያቱ ደግሞ በተለገሳቸው ደም በህይዎት ተርፈው ለዛሬ በመብቃታቸው ነው ይኽም የሠራዊታችንን የሕዝባዊነት ጥግ ያሳያልም ብለዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ደረጃ ሦስት ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አገኘሁ መንግስቴ በበኩላቸው የደም ልገሳው ዋነኛ ዓላማ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ያጋጠመውን የደም እጥረት ለመቅረፍ እና በዚህም ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሞት ለማስቀረት ነው ብለዋል።

በደም ልገሳው ከተሳተፉ አባላት መካከል ሻለቃ ጥላሁን ጌታቸው እንደተናገሩት በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የደም መፍሰሰስ እና በሱ ሳቢያ ሊጠፋ የሚችለውን ህይዎት ለመታደግ ደም በመለገሴ ደስተኛ ነኝ ብሏል። አስር አለቃ አሊ አብደላ በበኩሉ እኔ በውጊያ ቆስዬ ያገገምኩት እና ለዛሬው ቀን የበቃሁት በተለገሰኝ ደም ምክንያት በመኾኑ እኔም የሌላውን ህይዎት ለመታደግ ደም ለመሰጠት ወስኛለሁ ነው ያለው። ዘገባው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ነው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡
Next article“በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር