የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡

25

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠንካራ የግል ዳታ ጥበቃ ሥርዓት ለመፍጠር ያስችላል የተባለለት አዋጅ አጽድቋል፡፡ በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጁን አስመልክቶ እንደገለጸው አዋጁ የግል ዳታ ጥበቃ ተቆጣጣሪ ተቋምን በመሰየም ጠንካራ የግል ዳታ ጥበቃ ሥርዓት እንዲፈጠር ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

የግል ዳታን ማሰባሰብ አስፈላጊ እየኾነ መምጣቱ እና በዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የተሰበሰቡ የግል ዳታዎችን ማቀናበር ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው ሚና እያደገ በመምጣቱ አዋጁ እንደተዘጋጀ ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም ዳታ በሚሰበሰብበት እና በሚቀናበርበት ወቅት የግል ዳታ መብት ጥሰት እንዳይፈጠር ለመቆጣጠር የሚያስችል የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱም አዋጁ እንደተዘጋጀ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

በተጨማሪም አዋጁ ከግል ዳታ ጋር የተያያዙ የመብት ጥሰቶች ሲከሰቱ ውጤታማ መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም ከዳታ ማቀናበር ሥራ ጋር የተያያዘ አደጋን ለመቀነስ እና ኀላፊነት የሚሰማው ዳታ የማቀናበር ባሕልን ለማሳደግ ወሳኝ እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ የግል ዳታ ላይ መብትን በዝርዝር የሚደነግግ ሕግ ባለመኖሩ እና የግል ዳታ ጥበቃ ተቆጣጣሪ ተቋም ባለመሰየሙ ጠንካራ የግል ዳታ ጥበቃ ሥርዓት እንዳይፈጠር ማድረጉ ተነስቷል፡፡

በዚህም ዳታ በሚሰበሰብበት እና በሚቀናበርበት ወቅት የግል ዳታ መብት ጥሰት እንዳይፈጠር ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሕዝብ ጋር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መካሄዱንም ቋሚ ኮሚቴው ማስታወሱን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
Next articleበአማራ ክልል ያለውን የደም እጥረት ችግር ለመቅረፍ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች የደም ልገሳ አካሂደዋል።