የአማራ እና አፋር ክልሎችን በማገናኘት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሐይቅ – ቢስቲማ – ጭፍራ የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከ29 በመቶ በላይ ደረሰ።

39

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ እና አፋር ክልሎችን በማገናኘት ማኅበራዊ ትስስርን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው የሐይቅ – ቢስቲማ – ጭፍራ የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከ29 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገልጿል። ፕሮጀክቱ 74 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ነው።

2 ቢሊየን 233 ሚሊየን 149 ሺህ 775 ብር የተመደበለት ሲኾን ወጭውም የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ የግንባታ አፈጻጸም 29 ነጥብ 72 በመቶ ላይ መድረሱም ተገልጿል።

የግንባታውን ሂደት ለማሻሻል በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በኩል የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው። የመንገድ ግንባታውን እያከናወኑ የሚገኙት ፓወርኮን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና አሰር ኮንስትራክሽን በጋራ በመኾን ነው። የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን የሚያከናውነው ደግሞ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ነው።

አካባቢው ከዚህ በፊት ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ አውታር ያልተዘረጋበትና ለትራንስፖርት እንቅስቃሴም አስቸጋሪ እንደነበር ተገልጿል። ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ኅብረተሰብም ኾነ ለሀገር ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል፡፡

መንገዱ በዋናነት የአፋርና የአማራ ክልሎችን በቅርበት በማገናኘት ማኅበራዊ እድገት በማፋጠን ጥራት ያለዉ፣ ምቹ እና ፈጣን የኾነ የትራፊክ ፍስሰት እንዲኖር ከማስቻሉ ባሻገር በአካባቢው በስፋት የሚገኙትን ማሽላ እና የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶችን በማጓጓዝ የንግድ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ ያስችላል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕዝብን ጥቅም ለመጉዳት በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ሕግ የማስከበር ግዳጅን አጠናክረን እንቀጥላለን” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።