“የሕዝብን ጥቅም ለመጉዳት በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ሕግ የማስከበር ግዳጅን አጠናክረን እንቀጥላለን” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት

21

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ኮማንድ ፖስት ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት በተሰማራበት ቀጣና ሕግ የማስከበር ተልዕኮውን በብቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ አስታውቋል። ኮማንድ ፖስቱ ባደረጋቸው የኦፕሬሽን እና የስምሪት ሥራዎች የፅንፈኞችን የጥፋት ምኞት በማምከን በቀጣናው የሚኖረው ኅብረተሰብ ከስጋት ነፃ ሆኖ የልማት ሥራውን እንዲያከናውን ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

የቀጣናው ኮማንድ ፖስት እንዳስታወቀው ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በወሰዳቸው እርምጃዎች የፅንፈኞች መፈንጫ የነበረውን ዞን ነፃ ከማድረጉም ባሻገር በበርካታ ጽንፈኞች ላይም የእርምት እርምጃ ተወስዷል። በዚህ ሳምንት ብቻ 80 የፅንፈኛው አባላት እጅ ሲሰጡ 29ኙ ከነትጥቃቸው የገቡ መኾናቸውንም ኮማንድ ፖስቱ ጠቁሟል።

የፀጥታ ኃይሉ ባካሄዳቸው ኦፕሬሽኖች የዞኑ አሥተዳደር ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን፤ የመንግሥት እና የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ወደ ሥራቸው ተመልሰው ኅብረተሰቡን ማገልገል እንዲችሉ ተደርጓል። በዚሁ ጥምር የፀጥታ ኃይል ክትትል በአዋበል ወረዳ ለፅንፈኛ ቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ትላንት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

የኅብረተሰቡን ሰላም ለማፅናት ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ከመሥተዳድሩ እና ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ቀጣይነት ያላቸው ጠንካራ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል። “የሕዝብን ጥቅም ለመጉዳት በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ሕግ የማስከበር ግዳጅን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲልም ኮማንድ ፖስቱ አረጋግጧል ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ፡፡
Next articleየአማራ እና አፋር ክልሎችን በማገናኘት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሐይቅ – ቢስቲማ – ጭፍራ የመንገድ ፕሮጀክት ሥራ ከ29 በመቶ በላይ ደረሰ።