
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አግማስ ኢትዮጵያ እና ተቅዋ ሀበሻ ውሜንስ ግሎባል ኦርጋናይዜሽን ከዲኤንቪ ደሴ ጋር በመተባበር በዞኑ በተለያየ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የእለት ምግብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ከ47 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሊ ሰይድ ተናረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ16 ሺህ በላይ የሚኾኑት በመጠለያ ውስጥ ሲገኙ ቀሪዎቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ ይኖራሉ ነው ያሉት፡፡
ተፈናቃዮቹን የእለት ምግብ እንዲያገኙ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ኀላፊው በሚፈጠረው ክፍተትም የግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ተናረዋል፡፡ አግማስ ኢትዮጵያም በዞኑ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች በመንቀሳቀስ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የእለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ ማድረጉን አረጋግጠዋል፡፡
የአግማስ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ዳይሬክተር ኢንጅነር አብዱሰላም ሽፋው በጾም ወቅት የተፈናቀሉ ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ድጋፉ እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡ በገራዶ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የእለት ደራሽ የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በሀርቡ፣ በመቅደላ፣ በተሁለደሬ፣ በአርጎባ፣ በደሴ ዙሪያ ወረዳ እና በኮምቦልቻ ከተማ ደረቅ ወደብ መጠለያ ካምፕ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
500 የሚኾኑ ወላጆቻቸውን ላጡ ሕጻናትም የአልባሳት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ አግማስ ኢትዮጵያ ተቅዋ ሀበሻ ውሜንስ ግሎባል ኦርጋናይዜሽን ድጋፋን እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡ በአሰቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሕይወትን እያሳለፉ ያሉ ተፈናቃይ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመሥግነዋል፡፡ በዘላቂነት ወደቀያቸው ተመልሰው ወደነበረ የኑሮ ዘይቤያቸው እስኪገቡ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!