በተሠራ የተቀናጀ ሕግ የማስከበር ሥራ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።

24

ከሚሴ: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተሠራ የተቀናጀ የሕግ ማስከበር ሥራ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገልጿል። በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። የመድረኩ ዓላማ ሕዝቡን በማወያየት ክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦት በጋራ ለመፍታት ነው።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሸኔ እና የጽንፈኛ ኃይሎች በሚያደርጉት ያልተገባ እንቅስቃሴ ሕዝቡ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጡን በውይይት መድረኩ ተገልጿል። እንደ ክልል የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር የሚሠሩ አካላትን በማረም እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል በአካባቢው ሰላምን ማጽናት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነው ውይይት የተካሄደው

በውይይት መድረኩ የተገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሰላም እጦት ችግር መሰል የምክክር መድረኮች አስፈላጊ መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ መንግሥት የሕግ ማስከበሩን ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንዲሠራም ነው የጠየቁት። የከሚሴ ከተማ ከንቲባ ከድጃ አሊ ከተማዋ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት ብለዋል፡፡ የገጠመውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የሕግ ማስከበር ሥራ ስለመሠራቱም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡ በፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ በከተማዋ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ስለመቻሉም ነው ያብራሩት።

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ሐዋ አደም አካባቢው ለአሸባሪው ሸኔ እና ለጽንፈኛው ቡድን ተጋላጭ ቢኾንም በተሠራ የተቀናጀ ሕግ የማስከበር ሥራ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ስለመቻሉ ተናግረዋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም የተቀናጀ ሥራ እንደሚከናወን ኀላፊዋ ያስረዱት፡፡

ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ግንባታ 95 በመቶ ደረሰ።
Next articleበደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ፡፡