
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ የሚገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ግንባታ 95 በመቶ መድረሱን ከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል። ይህ የተገለጸው የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ እና መካከለኛ የሥራ ኀላፊዎች የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተመለከቱበት ወቅት ነው።
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቱ ተጥናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የከተማውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንደሚያዘምን ተናግረዋል። ዶክተር ማማሩ አያሌው ፕሮጀክቱ በዘመናዊነቱ በክልሉ ቀዳሚ ኾኖ እየተገነባ በመኾኑ ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ ይኾናል ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ፕሮጀክቱ በ300 ሚሊዮን ብር እየተገናባ ሲኾን ግንባታው 95 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተማው ያለውን ኋላቀር የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ከማዘመን አልፎ ለባዮ ጋዝ አገልግሎትም ይውላል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!