
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፑንትላንድ አዲስ የተመረጠው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ሞሐመድ ፋራህ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡ አምባሳደር ምስጋኑ የፑንትላንድ መንግሥት በቅርቡ ያካሄደውን ሰላማዊ ምርጫ አድንቀዋል። ኢትዮጵያ ከፑንትላንድ ጋር ያላትን ዘርፍ ብዙ ትብብሮች ለማጠናከር ቁርጠኛ መኾኗንም ገልጸዋል፡፡
የፑንትላንድ ልዑካን ኢትዮጵያ እና ፑንትላንድ የቆየ የወንድማማችነት ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለፑንትላንድ በጸጥታ እና በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ እና በፑንትላንድ መካከል በንግድ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና በሌሎች የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!