“የባለፈው ዓመት ሠልጣኞች ሁሉም ሥራ ይዘዋል” የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ

26

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት አወቀ ወጣ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣቱ እንደሚለው 12ኛ ክፍልን አጠናቅቆ የሥራ ማስተዋቂያዎችን ቢከታተልም ሥራ ማግኘት ግን አልቻለም። ወጣቱ አካባቢውን ሲቃኝ በቀበሌ ተደራጅተው ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች የሙያ ባለቤት ኾነው ተመለከተ። እሱም ቢረፍድም ሳይመሽበት ተደራጅቶ በቀበሌው ተገምግሞ በመመልመል የሕይዎት ክሕሎት ሥልጠና እየወሰደ እንደሚገኝ ነግሮናል።

“ሥልጠናውን መውሰዴ በዘፈቀደ የነበረውን የጊዜ አጠቃቀሜን በዕቅድ እንድመራው አድርጎኛል። እያደርም እራሴን ለመቀየር እና የተለያዩ የሥራ አማራጮችን ለመውሰድ አነሳስቶኛል” ብሏል። ወጣት አወቀ እክሎም በቀጣይ በኢንዱስትሪዎች የሥራ ላይ ሥልጣና ስለሚመቻችለት ጥሩ የጋራዥ ባለሙያ ኾኖ እንደሚወጣ እና የሥራ ባለቤትም እንደሚኾን ከወዲሁ ተስፋ ሰንቋል።

ሌላዋ ሠልጣኝ አዲሴ ተቀባ ትባላለች። 12ኛ ክፍልን ጨርሳ ሥራ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ብትሄድም ሥራ የውኃ ሽታ እንደኾነባት ትናገራለች። “አሁን እየተሰጠኝ ያለው ሥልጠና ሕይዎቴን በዕቅድ እንድመራ እና ከግቤ እንድደርስ ያደርገኛል” ብላለች። ወጣት አዲሴ የልብስ ስፌት ሠልጣኝ በመኾኗ በቀጣይም ለሥራ ላይ ልምምድ በተለያዩ ፋብሪካዎች ገብታ እንደምትሠለጥን ተነግሯታል። በመኾኑም የጥሩ ሙያ ባለቤት ስለምትኾን እሷ ሳትኾን ሥራ ወደ እሷ እንደሚመጣ ተስፋ አድርጋለች።

እየሩሳሌም ፈንታሁንም ትምህርቷን 12ኛ ክፍል ላይ ነው የጨረሰችው። ይሁን እና ሥራ ማግኘት ባለመቻሏ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈች ጠቁማ አሁን እየወሰደችው ያለው የሕይዎት ክህሎት ሥልጠና አንድ የልብስ ሰፌ ባለሙያ ሊኖረው የሚገባውን ዘርፈ ብዙ ባህርያት ስለሚያላብስ ለእኔ አዲስ የሕይዎት ምዕራፍ የምጀምርበት ነው ብላለች። ወደ ፊትም ከምታገኘው የሥራ ላይ ልምምድ ተጨምሮ “እጄ መልካም የልብስ ስፌት ባለሙያ ያደርገኛል” ነው ያለችው።

የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ፈለቀ ውቤ እንዳሉት ሠልጣኞቹ 1ሺህ 300 ሲኾኑ 800 ያህሉ ሴቶች ናቸው። የሕይዎት ክህሎት ሥልጠናውም ሰው ራሱን አውቆ ሌሎችንም ተረድቶ አገልግሎት እንዲሰጥ መሰረታዊ የሙያ ክሕሎትን ያጎናጽፋል፤ የሥነ አዕምሮ ፣ የሥራ ዝግጁነት እና የተግባቦት አቅምን ያጎለብታል ነው ያሉት።

ዋና ዲኑ ባለፈው ዓመት ከ1ሺህ 300 በላይ የሕይዎት ክሕሎት ሥልጠና ወስደው ለስድስት ወራት ያህል እንደየ ዝንባሌያቸው በተለያዩ ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች የሥራ ላይ ልምምድ ያደረጉ ሠልጣኞች ሁሉም የሥራ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። ኮሌጁ እስካሁን ከ4 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሕይዎት ክሕሎት ሥልጠና መስጠቱን ጠቁመዋል። በአማራ ክልል የወጣቶች የሕይዎት ክሕሎት ሥልጠና በተለያዩ ዙሮች በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ከተሞች እንደሚሰጥ ከባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው” የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት
Next articleበፑንትላንድ አዲስ የተመረጠው መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።