
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 95 በመቶ መድረሱን በቅርቡ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው። ከዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሀገሪቷ የኀይል ምንጭ ተስፋ መኾኑን አሳይቷል፡፡ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ አሁን በሀገሪቱ ያለውን 5 ሺህ 250 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦትን በእጥፍ ያሳድጋል። ለመኾኑ የግድቡ ግንባታ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ የሚኖረው ፋይዳ ምን ይኾን?
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንዳሉት ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት እያከናወነች የምትገኘው ሥራ የአፍሪካ ኅብረት አላማዎችን በማሳካት የድርሻዋን እየተወጣች መኾኑ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም እና ድርጅቱ ወደ ኅብረት እንዲያድግ ከፍተኛ ድርሻ እንደተወጣች ሁሉ አሁንም ኅብረቱ በ2063 ለማሳካት ያስቀመጣቸውን 20 ግቦች እየፈጸመች ትገኛለች ብለዋል። በተለይም ደግሞ 10ኛ ላይ የተቀመጠው አፍሪካን በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ግብን ቀድማ በመፈጸም ግንባር ቀደም ያደርጋታል።
ከዚህ ባለፈ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ ልማት በ2030 ለማሳካት ካስቀመጣቸው 17 ግቦች ውስጥ በሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ከንጹህ የኃይል ምንጭ ተደራሽ የማድረግ ግብ እየፈጸመች ትገኛለች። አሁን ባለው የኀይል አቅርቦት ብቻ ሳይኾን ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት እየሠራች መኾኑን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም እንዳሉት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ የኢትዮጵያን የወደፊት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጭምር የሚወስን ፕሮጀክት ነው፡፡
በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል እጥረት ለመቅረፍ ፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ማሽኖችን በመጠቀም ግብርናውን እንዲያዘምኑ ያግዛል። የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች ተቋማት አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ፋይዳው የጎላ ነው። ዘመናዊ ምድጃን በመተግበር ለማገዶ የሚውለውን ደን ከጭፍጨፋ ይታደጋል።
በ246 ኪሎ ሜትር ላይ በሚተኛው ሐይቅ የሚፈጠሩ 78 ደሴቶች የቱሪዝሙን መዳረሻ ያሰፋሉ። እስከ አሁን ከ300 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የጎበኙት ሲኾን ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
በዓመት ከ10 እስከ 20 ሺህ ቶን አሳ እንደሚመረትበትም ገልጸዋል። ይህም ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል የጀመረችውን ልማት ያሳድጋል። በግድቡ ዙሪያ ገባ የሚካሄደው አረንጓዴ ልማት ለአየር ንብረት መሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት። የውኃ ምርምር እና ጥናት ተቋማትን መገንባት ያስችላል። ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስር ይፈጥራል፤ ቀጣናዊ መረጋጋትንም ያመጣል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!