የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤትን ለተቀላቀሉ አባል ሀገራት አቀባበል ተደረገ፡፡

53

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤትን ለተቀላቀሉ አባል ሀገራት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ አቀባበል የተደረገላቸው የአንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኮትዴቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴዬ ባለፋት 20 ዓመታት ምክር ቤቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት እና የመጡ ለውጦችን ተናግረዋል። የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ሰፊ ጥረት ስለመደረጉ አስታውሰው፤ የተቋማት ግንባታ ላይም አዳዲስ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ ተደርገዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት እና ሌሎች የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ በመፍታት መሳሪያ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትን ለአብነት ጠቅሰዋል። የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በቀጣዮቹ 10 ዓመታትም በአህጉሩ ግጭቶችን መከላከል ላይ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ የሚሠራ መኾኑን አረጋግጠዋል።

በአባል ሀገራት የሚስተዋሉ ግጭቶች አሁንም መኖራቸውን ጠቅሰው በተለይም በሱዳን የቀጠለው ግጭት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። በአፍሪካ ሽብርተኝነትን መታገል፣ ሀገራት ለሰላም እና ጸጥታ በትብብር እንዲሠሩ ማገዝ፣ የዴሞክራሲ ባሕልን ማሳደግ እና ሌሎች ጉዳዮችም ቀጣይ ትኩረት ይሰጣቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2030 የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በትብብር እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤትን የተቀላቀሉ አባል ሀገራት ለሥራው መሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት ያሉት መኾኑ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቡሬ ዙሪያ ወረዳ በቁጭ ንዑስ ቀበሌ ስር የሚገኙ ሁለት አካባቢዎች ራሳቸውን ከጽንፈኛው ጥቃት መከላከላቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ ።
Next article“ግድቡ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው” የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት