
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የቡሬ ወረዳ አስተዳደር አቶ ሃይማኖት አሰፋ እንዳስታወቁት፣ በቁጭ ስር የሚገኙት ሶንቶም እና ቦቆጣቦ አካባቢዎች ከመከላከያ ሰራዊቱና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በቡሬ ዙሪያ ባሉት ሶንቶም እና ቦቆጣቦ ማኅበረሰብ ላይ ጽንፈኛው ቡድን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ከመፈፀም ባለፈ በርካታ ንብረት ዘርፏል፤ ሴት ወንድ ሳይል የጨፍጭፋ ተግባሩን ሕዝብ ላይ አሳይቷል ብለዋል፡፡
በቁጭ እና አካባቢው የሚገኙት እነዚህ አካባቢዎች ተደራጅተው የአማራ ሕዝብ ገዳዮች እና ዘራፊዎችን የማጽዳት ሥራ በሰፊው በመሥራት ቀጣናውን ከጽንፈኛ ነጻ ማውጣት ችለዋል ያሉት አቶ ሃይማኖት፣ አሁን ላይ በወረዳው ስር የሚገኙ ቀበሌዎች በፖሊስ እና በሚሊሻ የፀጥታ ሥራ እየሠሩ ኅብረተሰቡም ያለ ስጋት የእለት ኑሮው እንዲገፋ ማድረግ መቻላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነዚህ ሁለቱ ቀበሌዎች ጽንፈኛው በአሳቻ ሰዓት የፈፀመው ጭፍጨፋ እና የንብረት ዘረፋ ያስቆጣው ኅብረተሰብ ዳግመኛ በወረዳው እንደይደገም በአካባቢው ከሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች እና መሥተዳደሮች ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ዘመቻ መጀመራቸውንም ተናግረዋል ፡፡
ጽንፈኛው በተሳሳተ የማደናገሪያ ትርክቶች “የአማራ ሕዝብ ጥያቄ መላሽ እኔ ነኝ” ብሎ የተገዘተ ቢኾንም በተቃራኒው በመግደል፣ እገታ እና ዝርፊያ በመፈፀም በስቃይ አለንጋ ሕዝቡን ገርፎታል፡፡ በተለይም በሶንቶም እና ቦቆጣሞ ቀበሌዎች የፈፀመው ጭፍጨፋ እና ዝርፊያ ብሶት የወለደው ኅብረተሰብ እንዲፈጠር አድረጎታል ነው ያሉት፡፡
ኅብረተሰቡ ይህንን በታሪክ ገጥሞት የማያውቀውን ጥቃት ከመከላከያ እና ከአማራ የጸጥታ ኃይል ጋር በመጣመር እየተከላከለ ይገኛል። በእስካሁኑም መልካም ውጤት ማስገኘት ችሏል ብለዋል። መረጃው የጎጃም ኮማንድፖስት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!