
አዲስ አበባ: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአንዳንድ ቦታዎች እየፈረሱ ያሉ ህንፃዎች ሊፈርሱ የቻሉት ቅርስ ለመኾን የሚያስችላቸውን መስፈርት ባለማሟላታቸው መኾኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በፒያሳ እና አካባቢ በመንገድ ዳር ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ ታሪካዊ ይዘት ባላቸው ህንፃዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለሥልጣኑ በአንዳንድ ቦታዎች እየፈረሱ ያሉ ህንፃዎች ሊፈርሱ የቻሉት ቅርስ ለመኾን የሚያስችላቸውን መስፈርት ባለማሟላታቸው መኾኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በሚያከናውነው የልማት ፕሮጀክት ላይ ህንጻው ለመቆየት የተገነባበት ዘመን፣ ውጫዊ እና ውስጣዊ ዲዛይኑ፣ ኪነ-ህንፃው፣ ታሪካዊ ዳራው እና ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት ሊኖርባቸው ይገባል ብለዋል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ 147 ያህል ህንፃዎች በ2013/14 ዓ.ም በተካሄደ ምዝገባ በቅርስነት ተመዝግበው የነበረ ቢኾንም ከግማሽ በላይ የሚኾኑት ግን የቅርስነት መስፈርት አያሟሉም ነው ያሉት። የቅርስ ጥበቃው እና ልማቱ መጣጣም ስላለበት ቅርስ ባለሥልጣን ቁጥጥር እና ክትትል እያደረገ መኾኑን ረዳት ፕሮፌስር አበባው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!