
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2016/17 የመኸር ወቅት የክረምት ሥራዎች ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ መሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት የነበረውን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። ዘንድሮ የግብዓት አቅርቦት በጊዜው እየቀረበ መኾኑ ለምርት እና ምርታማነት መጨመር ታላቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ማደበሪያዎችን በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን እንጨምራለን ነው ያሉት። ከባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ለማምረት የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴን አጠናከረው እንደሚቀጥሉ እና የግብርና መመሪያዎችን እንደሚተገብሩም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው ግብርና የክልሉን ከፍተኛ ምጣኔ ሃብት የሚሸከመው ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል። ክረምት ላይ የሚሠሩ የሰብል ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ትልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው እና ሰፊ ሽፋን የሚይዙ መኾናቸውን ተናግረዋል። በክረምቱ ወቅት የተሻለ ለመሥራት ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ ከቀበሌ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች ጀምሮ ውይይት መደረጉን ነው የገለጹት። እስከታች ድረስ ለመተግበር የሚያስችሉ የግብርና ቤተሰቦች መገኘታቸውንም ተናግረዋል። ውይይቱ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ልምድ የሚወሰድባቸውን በመውሰድ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ ለመሥራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። በክልሉ 5 ነጥብ 18 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል። የሚታረሰው መሬት ከባለፈው ዓመት በ63 ሺህ ሄክታር ጭማሬ እንዳለውም ተናግረዋል።
ከሚታረሰው መሬት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ መታቀዱንም ገልጸዋል። እቅዱን ለማሳካት ሥራዎችን ግልጽ እና ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። በዓመቱ እቅዱን ለማሳካት ይሠራልም ብለዋል። የባለፈውን ዓመት የግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት ሊፈታ የሚችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። መንግሥት ለግብዓት አቅርቦት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ግብዓት ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች ቅድሚያ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የግብዓት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። በምርምር የተደገፉ ምክረ ሀሳቦችን መተግበርም ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት። 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን ገልጸዋል። ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚልቀው ማዳበሪያ ደግሞ ወደ አርሶ አደሮች ለማድረስ ጥረት ተደርጓል ነው የተባለው።
የግብዓት አቅርቦት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ከገባበት ጊዜ እና ከገባው ብዛት አንፃር የተሻለ መኾኑንም ተናግረዋል። ለምርት እና ምርታማነት ነባራዊ ሁኔታውን ተቋቁሞ መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። የምርጥ ዘር አቅርቦትም እየተጓጓዘ ነው ተብሏል። ባለፉት ዓመታት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተሻለ ሥራ መሠራቱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው 1 ሺህ 800 ትራክተሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። ትራክተሮችን በሚገባ መጠቀም ይገባልም ብለዋል።
ግብርናውን በግብዓት እና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራው እንደሚጥልም አስታውቀዋል። ባለሙያዎች እና መሪዎች የሚቀርበውን ማዳበሪያ በፍጥነት ማሰራጨት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ሥርጭቱ ፍትሐዊ መኾኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!