የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን አሳለፈ።

115

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን 2017-2021 የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚና ፊሲካል ማዕቀፉ የመንግስት በጀት ከማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታው እና የፊሲካል አቅም ጋር ተጣጥሞ እንዲዘጋጅ ለማድረግ፤ ከመንግሥት ገቢ አሰባሰብ እና ሀብት አመዳደብ አኳያ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማመላከት ለቀጣይ በጀት አመት የበጀት ዝግጅት ለማድረግ፤ የመካከለኛ ዘመን የመንግሥት ገቢና ወጪ እንዲሁም የፊሲካል ሚዛን የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመለየት እና ለማመላከት የሚያገለግል ማዕቀፍ በመሆኑ ምክር ቤቱ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የእኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የተደረጉ ለውጦችን በሕግ ማእቀፉ ውስጥ ማስገባት በማስፈለጉ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ጫና እንዳያርፍባቸው ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብዓቶችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article500 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው፡፡
Next article“በአማራ ክልል በመኸር ወቅት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል” ግብርና ቢሮ