500 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው፡፡

32

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለ2016/2017 የምርት ዘመን ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሩ በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። ዘንድሮ ካለፈው ዓመት በተሻለ ማዳበሪያ ቀድሞ መግባቱ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ሥራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ ኀይለየሱስ ዳምጤ እንደተናገሩት አርሶ አደሮች የቀጣይ መኸር ወቅት ሰብል ልማት ሥራውን ወቅቱን ጠብቆ እንዲያከናውን ማዳበሪያ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በ2016/2017 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ግዥ ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ እንደኾነ ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ግማሽ ሚሊዮን ማዳበሪያ ወደ ዞኑ አጓጉዞ ማድረስ ተችሏል። ከቀረበው ውስጥም 148 ሺህ ኩንታሉን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በዞኑ የአፈር ማዳበሪያ የገባው ጥር/2015 ዓ.ም ላይ እንደነበር ያስታወሱት ቡድን መሪው፤ ዘንድሮ ከሕዳር/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየቀረበ መኾኑን ተናግረዋል።

ማዳበሪያውን በጎዛምን፣ ሞጣ እና ጊወን የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን እንዲሁም በመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በማራገፍ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ቀሪውን ማዳበሪያም በፍጥነት ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። በዞኑ የጎዛምን ወረዳ አርሶ አደር ባለው ጊዜ ሙሉቀን እንዳሉት ለመጪው የመኸር ወቅት ለሰብል ልማት የሚውል ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ መውሰድ ችለዋል።

የወሰዱትን ማዳበሪያ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ለመጠቀም ማቀዳቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ማዳበሪያው ወቅቱን ጠብቆ መግባቱ ለግብርና ሥራው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። በዘንድሮ ዓመት ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ማዳበሪያው ቀድሞ መግባቱ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ሥራ ለማከናወን ያስችላል ያሉት ደግሞ የአነደድ ወረዳ አርሶ አደር ማስረሻ ደግሰው ናቸው።

ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ እጥረት በማጋጠሙ እና ዘግይቶ በመግባቱ በግብርና ሥራው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ቀድሞ በመግባቱ ችግሩ መቃለሉን ተናግረዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቦ ጥቅም ላይ ውሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብርና ከፖለቲካ በላይ ነው፤ ግብርና የሕልውና ጉዳይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔዎችን አሳለፈ።