
ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2016/17 የመኸር ወቅት የክረምት ሥራዎችን የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው። በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ መሪዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ግብርና የልዕልና መገለጫ ጉዳይ መኾኑ ተነስቷል። የግብርና ግብዓት ሥርጭትን ፍትኃዊ በማድረግ ግብን ማሳካት እንደሚገባም ተመላክቷል። በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተሰባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ ( ዶ.ር) “ሰላም ለግብርና ግብርና ለሰላም ወሳኝ ነው” ብለዋል። በክልሉ የግብርናውን ሥራ ማፋጠን ብቻ ሳይኾን የተረጋጋ አካባቢ እና ለልማት የሚተጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የግብርና ባለሙያዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። የተፈጠረው ውስብስብ ችግር በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ይገኛል ተብሎ ከተያዘው የምርት እቅድ 15 ሚሊዮን ኩንታል መቀነሱን ያነሱት ዶክተር ድረስ የግብርና ባለሙያዎች በሰላም ተንቀሳቅሰው አለመሥራት፣ በክልሉ የተፈጠረው የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የተፈጠረው ግጭት እና ድርቅ ለምርት መቀነሱ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው በችግር ውስጥ ኾነን መስዋዕትነት ከፍለን የአማራ ክልል አርሶ አደሮችን ጥያቄ መመለስ፣ ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ አለብን ነው ያሉት።
ችግሮቹን በመቋቋም በጦርነት እና በሌሎች ጉዳዮች የተጎዳውን የግብርና ልማት ማካካስ እንደሚገባም አሳስበዋል። ባለፉት ዓመታት የገጠሙን ችግሮች ሊያካክስ በሚችል መንገድ በንቅናቄ እና በተቀናጀ መንገድ ሥራችንን መፈጸም ይገባል ነው ያሉት። ምን መሥራት እንዳለብን ተግባብተን መሥራት አለብን ብለዋል።
በመግባባት የግብርና አብዮት መፍጠር አለብን ያሉት ኀላፊው “ግብርና ከፖለቲካ በላይ ነው፤ ግብርና የሕልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል። ግብርና ንጹሕ አስተሳሰብን የሚጠይቅ፣ ከውርደት የሚታደግ፣ ክብርን የሚያጎናጽፍ መኾኑንም ገልጸዋል። ግብርናን ከፍ አድርጎ መረዳት እና ከሌሎች አስተሳሰቦች ጋር መቀየጥ እንደማይገባም አሳስበዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት አርሶ አደሮችን በማነቃነቅ የምርት አብዮት ለመፍጠር መግባባት አለብን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!