ለሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ፤ ለጎረቤት ሀገራት ደግሞ የብርሃን ተስፋ የተጣለበት ግድብ!

28

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ እንደሚጠቁመው አሁን ላይ የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት 5 ሺህ 250 ሜጋ ዋት ሲኾን 96 በመቶ ኃይል የሚመነጨው ደግሞ ከውኃ ነው፡፡ ቀሪው ከነፋስ እና ደረቅ ቆሻሻ የሚመነጭ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የኃይል ተጠቃሚውን ቁጥር ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንዳሉት

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ፣ የአሰላ የነፋስ ኃይል እና አይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሙሉ በመሉ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ7 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ያመነጫሉ። አሁን ያለውን የሀገሪቱን አጠቃላይ የኃይል አቅርቦትም ከ12 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ያደርሱታል። በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች ውስጥ ደግሞ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት በማመንጨት የላቀውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኃይል እስከ 13 በመቶ የሚኾነውን ወደ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ኤክስፖርት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከዚህም በዓመት 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ታገኛለች። በቀጣይም የተጀመሩ ኃይል ማመንጫዎች ሲጠናቀቁ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ሌሎች ሀገራት ኤክስፖርት ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። የተለያዩ ሀገራትም ከወዲሁ ፍላጎት ማሳየታቸውን አንስተዋል።

ከታኅሳሥ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ኬንያ የመላክ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን በማሳያነት አንስተዋል። ታንዛኒያ እና ሌሎች አጎራባች ሀገራትን ጨምሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ለማቅረብ በእቅድ ተቀምጧል። ለዚህ ደግሞ ለአዲስ መሠረተ ልማት ተጨማሪ ወጭ ማውጣት ሳያስፈልግ አሁን ባለው መሠረተ ልማት ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል። አሁን ያለው መሠረተ ልማት እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት ማስተላለፍ እንደሚችል ያነሱት ዳይሬክተሩ እያስተላለፈ የሚገኘው ግን 200 ሜጋ ዋት ብቻ መኾኑን ነው የገለጹት።

የሕዳሴው ግድብ አጠቃላይ ከሚያመነጨው ግማሽ ያህሉን እንኳ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢቻል በዓመት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሊገኝ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ከኃይል ሽያጭ በሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በሁሉም ክልሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያ እየተሠራ እንደሚገኝ ያነሱት ዳይሬክተሩ የባሕር ዳር – ወልዲያ – ኮምቦልቻ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክትን በማሳያነት አንስተዋል። ፕሮጀክቱ የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚመልስ ቢኾንም ባለፉት ዓመታት በተከሰቱት የኮሮና ቫይረስ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና በሚፈጸመው ስርቆት በወቅቱ ተጠናቅቆ ለታለመለት አላማ እንዳይውል አድርጓል።

በተለይም ደግሞ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ስርቆት ሀገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጋት መኾኑን ገልጸዋል። ችግሩን ማኅበረሰቡ ከፍትሕ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በባለቤትነት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋሎ።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ በቀጣይ፦

👉 የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት

👉 የኮይሻ የኀይል ማመንጫ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት

👉 የአሰላ የነፋስ ሃይል 100 ሜጋ ዋት

👉 አይሻ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት በማመንጨት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ ዓባይ ግን ሁሉን ድል አደረገው”
Next article“ግብርና ከፖለቲካ በላይ ነው፤ ግብርና የሕልውና ጉዳይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)