“ ዓባይ ግን ሁሉን ድል አደረገው”

50

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)  ባፈለቀችው ወንዝ ተዘመተባት፣ ባፈለቀችው አፍላግ ጦርነት ተከፈተባት፣ ጎራዴ ተሳለባት፣ ጦር ተሾለባት፣  ጠላት በዛባት፡፡ አፍልቃ በሰጠች አያሌ መከራዎችን ተቀበለች፣ የፈተና ዘመናትን አሳለፈች፤ በሃብቷ በመጣባት ጦርነት ታላላቅ ጦርነቶችን ገጠመች፡፡ ለክብር ሲባል ልጆቿን ገበረች፡፡

ጀግኖቹ ክብራችን፣ ሀገራችን፣ ሉዓላዊነታችን፣ ነጻነታችን፣ ሃብታችን አናስነካም ሲሉ ተዋደቁላት፣ ከግዳይ ላይ ግዳይ እየደራረቡ፣ ከድል ላይ ድል እጨመሩ ጠላቶቿን ቀጡላት፤ ግዮንን (ዓባይን) ያሉ የበረሃ ሀገር ነገሥታት ዘመን በገጠማቸው፣ ጉልበት በደረጀላቸው ጊዜ ሁሉ  የምትናወጥ እየመሰላቸው በኢትዮጵያ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ላኩባት፣ እንኳን ለፎከረ ለወረወረ አትደነግጥምና ዛቻውን ችላ ስትልባቸው ጦር ያዘምቱባታል፤ ጦሩንም እንዳልነበር አድርጋ ትመልሰዋለች፡፡

ዓባይን ያሉ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ አያሌ ደባዎችን ሠሩባት፣ ይቆርሷት፣ ይከፍሏት ዘንድ ዶለቱባት፣ አንድነቷን አሳጥተው፣ ነጻነቷን ነጥቀው ሃብቷን ይቀራመቱ ዘንድ የጦር ችንካር አበዙባት፤ ኢትዮጵያ ግን ችንካሮቹን ነቀለቻቸው፣ ደባዎችን አፈረሰቻቸው፣ ጠላቶቿን እጅ አስነሳቻቸው፡፡ 

አፈር እና ውኃዋን ስትገብር የኖረች ሀገር ወንዝሽ የአንቺ አይደለም፣ አፈርሽም ከአንቺ አይደለም ስትባል ኖረች፣ እርሷ እያበራች ሌሎች ይበላሉ፣ እርሷ እየቀለጠች ሌሎች ይኖራሉ፣ እርሷ እየተሸረሸረች ሌሎች በአፈር ይመላሉ፡፡ ይህ ለዘመናት ዘለቀ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንዛቸውን ሳይጠቀሙበት፣ በጌጣቸው ሳያጌጡበት ዘመናት ሄደው ዘመናት ተተኩ፡፡ ሌሎች በኢትዮጵያ ሃብት ታወቁበት፣ ሌሎች በኢትዮጵያ ሃብት ኀያል ኾኑበት፣ ተሰሚነታቸውን ከፍ ከፍ አደረጉበት፡፡

ከአያሌ ዘመናት በኋላ ግን ኢትዮጵያውያን ሃብታቸውን ይጠቀሙበት፣ ጌጣቸውን ያጌጡበት ዘንድ ወደዱ፡፡ የወደዱትንም አደረጉ፡፡ ዓባይን ገደቡ፡፡

ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት እንደተባለ፣ ዓባይ ደግሞ የኢትዮጵያ ስጦታ ነው፣ ኢትዮጵያ የዓባይ መፍለቂያ ጓዳ ናትና፡፡

ግድቡ ዓባይ የግብጽ ብቻ ነው ብሎ ሲያምን የነበረውን የዓለም ሕዝብ ሻረው፣ ትክክለኛውን እውነታ ገለጠው፤ ዓባይን የነካ ወዮለት ሲባል የነበረውን ማሰፈራሪያም እንዳልነበር አደረገው፤ ከቃል የዘለለ አንዳልኾነ አሳየው፤  ዓባይ ሁሉን ነገር ድል አደረገው፡፡ ኢትዮጵያ አትችልም የተባለውን እንድምትችል አሳየው፡፡  በኢትዮጵያ ላይ ተሟረተባት፣ ተዛተባት ዓባይ ግን ሁሉንም ድል አደረገው፡፡ 

በሐዋሳ ዪኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፍልስፍና መምህር  አወል አሊ ከዓባይ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ኢትዮጵያ በዓባይ ፖለቲካ ኀያል ናት፤ የግብጽ እና የሱዳን የዓባይ ፖለቲካ የበላይነት ያከትማል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ጉልበቷን፣ ተሰሚነቷን፣ በውድቀት ውስጥ ትንሳኤዋን አሳይታለች ይሏታል፡፡ በውስጧ ብዙ ትርምሶች፣ ብዙ ችግሮች አሉ ዓባይ ግን በውድቀቷ ውስጥ ትንሳኤዋን ያሳየችበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ  በቅኝ ግዛት ዘመን ውል የተገቡ አሳሪ ስምምነቶችን እና ማነቆዎችን ሁሉ ሰባብራ ታላቅ ፕሮጄክት ምሥራቅ አፍሪካ ላይ አስቀምጣለች፡፡  የጻፉት ሕጉ ሳይቀየር፣ ወረቀቱ እያለ፣ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በጸጥታው ምክር ቤት ብዙ ጊዜ ሥብሠባ ተጠርቶበት ያልቆመ ታላቅ ግድብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እምቢተኝነት እና ሥራ መቀጠል ግድቡ ሳያልቅም የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ ማድረጉ አንደኛው ማሳያ ነው ይላሉ መምህሩ፡፡

እንደ መምህሩ ገለጻ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና  በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች  ያደረጉት ግድቡ የኔ ነው የሚል ዘመቻ ታላቅ ተጽዕኖ የፈጠረ ነው፡፡ ግድቡ የመቻቻል፣ የማድረግ፣ የሉዓላዊነት ምልክት መኾኑን አሳይቷል፤ ችግር ቢኖር እንኳን ለግድቡ በጋራ መቆምን አሳይተናል፤ በሌላ ጉዳይ በአንድ ላይ የማይቆሙ ሰዎች ለግድቡ በአንድ ላይ ሲቆሙ ተመልከተናል፤ በሌላ ጉዳይ ደካማ ብንኾን እንኳ በግደቡ ጉዳይ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በአንድነት ተነስተናል፤ ይህ አንድነትን ከፍ ያደረገ ነው፤ አንድነት ከፍ ካለ ደግሞ ተስሚነት ከፍ ይላል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ኾና አሁንም በድፍረት ታላላቅ ፕሮጄክቶችን መፈጸም የምትችል፣ ተሰሚነት ያላት ሀገር መኾኗን በትክክል አሳይታለች ይላሉ፡፡ በግድቡ ምክንያት መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ግለሰቦች የኢትዮጵያን ድምጽ ለዓለም አሰምተዋል፤ በዓባይ ግድብ ምክንያት የኢትዮጵያ ድምጽ ተሰምቷል፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ደግሞ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ከዚህ የላቀ ከፍ ይላል ብለዋል መምህሩ፡፡

ታላላቅ ምሁራን የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ ሞግተዋል፤ የዓባይ ግድብ በናይል ላይ ተመስርተው ሕይወታቸው የተመሠረተው እነ ግብጽ እንጂ ሌሎች አይደሉም የሚለውን የተዛባ ትረካ የቀየረ ነው ይሉታል፡፡ ይሄም የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርገው ነው፡፡ በዓባይ ( ናይል) ላይ የውሸት ትርክት አለ፤ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ላይ አምልኮ ሁሉ ያላቸው ናቸው፤ ይሄም ዓባይን ከውኃ በላይ የሚያስብ ማኅበረሰብ እንዳለን የሚያሳይ ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ  ከውኃ ጋር መንፈሳዊ ቁርኝት አለው ብለን መተንተን አልቻልንም ነው ያሉት፡፡

ግብጾች ግብጽ ማለት ናይል ነው፤ ናይል ማለት ግብጽ ነው የሚል የማይነጣጠል ማሰሪያ አንቀጽ አላቸው፤ እኛ ግን በዛ ልክ የሚኾን የለንም፤  ዓባይን በሥነ ጽሑፍ እና በሌሎች ዘርፎች ስናሳይ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ከፍ ይላል ነው የሚሉት፡፡ የዓባይ ግድብ ሳይፈጸም ገና የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል፤ ጮኸቱ እና ግርግሩ ቀዝቅዟል፤ አስቀድሞ ገና ኢትዮጵያ ደሀ ናት በብድር ነው የምትሠራው ሲሉ፣ በራሳችን ሃብት ሠራነው፣ ይሄም የነበራቸውን ግምት እና እሳቤ አፈረሰው፤ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጉልበት ይሄ  ነበር ይላሉ መምህሩ፡፡

የራስን በራስ መሥራት ኢትዮጵያውያን ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ፣ ተደማጭነትን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ የዓባይ ግድብ የኅብረት፣ አብሮ የመቆም፣ ችግርን የመቋቋም፣ ለልማት መታተርን የሚያሳይ የኅብረት ገመድ፣  የአንድነት ድርና ማግ ነው ብለዋል፡፡  አንድነት እስካለ ድረስ የትኛውም ኀይል ጀሮ ሰጥቶ ያዳምጣል፤ መበታተን እስካለ ድረስ ጩኸቱ ቢበዛም ማንም አይሰማም፡፡ የሕዳሴ ግድም ዜጎችን ያሠባሠበ፣ የተለያዩ እይታዎችን ወደ አንድ ቋት ያመጣ፣ የማይተያዩ ፊቶችን ፊት ለፊት ያቆመ፣ አብረው የማይቆሙ ሰዎችን አንድ ላይ ያጣመረ በመኾኑ የኢትዮጵያን ተሰሚነት በብዙ ዘርፉ ከፍ የሚያደርግ ነው ይላሉ፡፡

እንደ መምህሩ ገለጻ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የመደራደሪያ ዋስትና ነው፤ ኢትዮጵያ እስካሁን በዲፕሎማሲ ያላሳካቻቸውን ስኬቶች እና ያጣቻቸውን እድሎች በሕዳሴ ግድብ ታሳካለች፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኛ አንደኛው የመከራከሪያ አጀንዳ እና ዋነኛ ተያዥ ነው፡፡ የባሕር በር ያላቸውን ሀገራት እናንተም ከዓባይ ውሰዱ ለእኛም የባሕር በር ስጡን ማለት ይቻላል፡፡ ዓባይ ብቻ አይደለም ሌሎች ወንዞችም የኢትዮጵያ የባሕር በር መደራደሪያ ይኾናሉ ነው የሚሉት፡፡

ለጎረቤት ሀገራት የንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞች ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኛ መንገድ ይኾናሉ፡፡ ንፁሕ ውኃ መጠጥን ከኢትዮጵያ የሚያገኙ ሀገራት ለኢትዮጵያ የባሕር በር አንሰጥም አይሉም፡፡ የሚጠበቀው የባሕር በር ማግኛ አማራጮችን ማስፋት ብቻ ነው፡፡ ከዓባይ ግድብ የሚወጣው የኤልክትሪክ ኃይል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ኢንዱስትሪን የሚያስፋፋ፣ እጣ ፈንታው ሕዳሴ ግድቡ ላይ የተንጠለጠለ ሕዝብ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነውም ብለዋል፡፡

ብዙዎች ምኞታቸው ደካማ እና ተልፈስፋሽ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ መፍጠር ነው፣ ዋናው ዓላማቸው ኢትዮጵያን በተለያዬ መልኩ ማሽመድመድ ነው፤  የህዳሴ ግደቡ ግን የሀገራትን ጩኸት፣ የጸጥታው ምክር ቤትን ሥብሠባ፣ የግብጽን ጋጋታ፣ የሱዳንን ወላወይነት፣ በሀገር ውስጥ ያለውን ባንዳ ሁሉ ያሸነፈ ነው ይላሉ፡፡ የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅማቸው ሲመጡባቸው ሊገለጥ የሚችል እና የኢትዮጵያ ጀግንነት ድንገት የሚፈነዳ መኾኑን ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ ኢትዮጵያ በብዙ ግርግር ውስጥ ኾና አሁንም ገናና፣ አሁንም ነጮች የማያንበረክኳት፣ ሌላ ሀገር ጥቅሟን የማይቀማት፣ አሁንም ቢኾን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ወደኋላ የማትል ሀገር መኾኗንም ያስመሰከረ ግድብ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ተሰሚነት፣ የሕዝቦቿን አንድነት የሚያመጣ፣ የፖለቲካ ተሰሚነትን የሚያሳድግ ነው የዓባይ ግድብ፡፡

ዓባይ ግን ዛቻውን ዘጋው፤ ሁሉን ነገር ድል አደረገው፡፡ ዓባይ ውሸትን የቀበረ፣ እውነትን ያነጠረ ሕያው ምስክር ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

👇ቀጣዮችን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን የአሚኮ ቤተሰብ ይሁኑ
ድረገጽ www.ameco.et
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
ረምብል https://rumble.com/c/c-4646842
ቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ኤክስ (ትዊተር) https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://www.tiktok.com/@ameco.et
ኢንስታግራም https://instagram.com/ameco.et
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://bit.ly/48iEHRC
አሚኮ ስፖርት https://bit.ly/3rkHxVF
አሚኮ እውነታ ማጣሪያ http://bit.ly/469N8wG

Previous articleኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው መስኮች የጋራ ሥምምነት አካሄዱ።
Next articleለሀገር ትልቅ የገቢ ምንጭ፤ ለጎረቤት ሀገራት ደግሞ የብርሃን ተስፋ የተጣለበት ግድብ!