
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ አዲሱ አረጋ በቻይና ኒንሺያ ግዛት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጸሀፊ እና የኒንሺያ ሕዝቦች ጉባኤ ሊቀመንበር ሊያንግ ያንሹ ጋር ተወያዩ። ውይይታቸውም በአራት ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።
የመጀመሪያው ብልጽግና ፓርቲ እና የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ በስልጠና፣ በተሞክሮ እና ልምድ ልውውጥ አብሮ ለመሥራት የጀመሯቸውን ጥረቶች ወደ ተግባራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። ከዚህ በፊት በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግንኙነቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል። በተለይ ከፓርቲ አባላት እና አመራሮች አቅም ግንባታ አንፃር ያሉ ተቋማት ከብልፅግና አቻ ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሁለተኛው ስምምነት ላይ የደረሱት በመሠረተ ልማት ግንባታ እና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ አቅምን በመገንባት ረገድ ሲሆን በኢንቨስትመንት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን፣ በግብርና እንዲሁም በአይሲቲ ላይ የሚደረጉ የመዋእለ ንዋይ ፍሰቶች ይበልጥ እንዲጨምሩ እና ይበልጥ ለማስተሳሰር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሦስተኛው በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅት የጋራ መግባባት የተደረሰበት በክልሎች እና በከተሞች መካከል ያለ የእህትማማችነት ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠልን የተመለከተ ነው ተብሏል። ከዚህ በፊት የኒንሺያ ግዛት ከኦሮሚያ ክልል ጋር የመሠረተችውን የእህትማችነት ጥምረት በማጠናከር ከሌሎች ክልሎች እና ከተሞች ጋርም ለመመሥረት ተስማምተዋል።
የከተሞች ለከተሞች ግንኙነትን ማሳደግ የባህል ትውውቅን ከማጎልበት በላይ አዳዲስ እድሎችን እንደሚፈጥር እና በቀጣይ የሁለቱ ፓርቲዎች የቤት ሥራ እንደኾነ ተነስቷል። በመጨረሻም በባሕል፣ በቱሪዝም እና በማኅበራዊ መስኮች ተባብሮ ለመሥራት ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የረጅም ታሪክ ባለቤት እንደሆነችው ሁሉ ኒንሺያ ግዛትም ከቻይና ስልጣኔ መገኛዎች አንዷ በመኾኗ በዚህ መስክም አብረው ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል። በትምህርት፣ በማኅበረሰብ ግንባታ፣ በወጣቶች ባሕል ልውውጥ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው መክረዋል።
በኢትዮጵያም ኾነች ኒንሺያ ራስገዝ ግዛት ያለው የቱሪዝም አቅም ከፍተኛ እንደኾነ እና ይህንንም ይበልጥ አውጥቶ ለመጠቀም በትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ሊንግ ያንሹ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበረ ሲሆን በቆይታቸው ለተደረገላቸው ደማቅ መስተንግዶ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አቶ አዲሱም በበኩላቸው ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገው መስተንግዶ ያላቸው አክብሮት የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!