“የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሁለት ፕሮጀክት መንገድ ጠራጊ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

48

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሁለት ጋር በትብብር ሲሠራው የነበረውን ፕሮጀክት ለአርሶ አደሮች በማስረከብ የማጠናቀቂያ ፕሮግራሙን በባሕር ዳር አካሂዷል፡፡ በማጠናቀቂያ ፕሮግራሙ ላይ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ የቢሮ ኀላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል፡፡

ወይዘሮ በላይነሽ መጋቢ በሰሜን ወሎ ዞን የግዳን ወረዳ 09 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሯ በተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሁለት ላይ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም ወደ ወረዳው ከመግባቱ በፊት ከዓመት አንድ ጊዜ የሚያመርቱት አርሶ አደር በላይነሽ ዛሬ ከዓመት ሦስት ጊዜ እያመረቱ ቤታቸውን ሙሉ አድርገዋል፡፡ በልቶ ከማደር ወጥተው ዛሬ ለሽያጭ የሚያቀርቡት ምርት የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ አራት ቤተሰብ የሚያሥተዳድሩት እናት ልጆቻቸውን በአግባቡ እያስተማሩም ነው፡፡

በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ በክረምት ስንዴ እና ጤፍ በመስኖ ሽምብራ፣ ጓያ፣ ነጭ ሽንኩርት ያመርታሉ፡፡ ከዚህም በዓመት እስከ 190 ሺህ ብር ነጭ ሽንኩርት ብቻ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ ሥራውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው አርሶ አደር ጀጃው ሰፈፈ ይባላሉ፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምዕራብ በለሳ ወረዳ አርባያ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በፕሮጀክቱ ውስጥ ባለቻቸው አንድ ገመድ መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡ ለልጃቸው ባጃጅ ገዝተዋል፣ መኖሪያ ቤት ገዝተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ ቀበሌያቸው ከመጣ በኋላ አካባቢያቸው ከጥቁር ደም ርቆ ሁሉም ምርት ላይ ብቻ አተኩሯል፡፡ አሁን በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር እንደሚሸጡም ያነሳሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ከአርሶ አደሮች ባሻገር በአካባቢው ለሚኖረው ሥራ አጥ ወጣት የሥራ እድል በመፍጠሩ ሌብነት ከአካባቢያችን ተወግዷል ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርና እና የአየር ንብርት ሽግግር ፕሮግራም ማናጀር በለጠ ጌታሁን ፕሮግራሙ ዝቅተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ በሰባት ዞኖች በ21 ወረዳዎች አነስተኛ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት አርሶ አደሮች ከዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ እንዲያመርቱ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ዓላማ ይዞ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም ከ6 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ሊያለማ የሚችል 33 የመስኖ አውታሮችን በመገንባት ከ12 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ ከመስኖ አውታር በተጨማሪ በተፋሰስ ልማት፣ በአግሮ ቢዝነስ፣ በገበያ ልማት፣ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የመስኖ ማኅበር በማቋቋም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) በተገኘ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት የግብርና ደጋፊ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን የገለጹት ኀላፊው የአፈር ለምነትን በመጠበቅ እና የተፋሰስ ልማትን በማጠናከር የአርሶ አደሮች የተፋሰስ ልማት ማኅበር እንዲቋቋም በማድረግ እና የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል መሳተፉን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ከራስ አልፎ ለገበያ የሚኾኑ ምርቶችን እንዲያቀርቡ ያደረገ ፕሮጀክት መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ዶክተር ድረስ ፕሮጀክቱ “መንገድ ጠራጊ ፕሮጅክት ነው” ብለዋል፡፡ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሁለት የቆይታ ጊዜውን አጠናቅቆ ቢወጣም ዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ላይ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ድረስ እንዳሉት የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ሁለት በቆይታው ግብርና ቢሮ ያወጣቸውን ፖሊሲዎች እና ስትራቴጅዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስቸግሩትን የግብዓት፣ የዕውቀት እና የገንዘብ ችግር በመቅረፍ ሲሠራ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡ሥራው ወደ መደበኛ የግብርና ሥራ እንዲገባ በማድረግ ዘላቂነቱን ለማስቀጠል እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማርሽ ቀያሪ ትውልድ ደማቅ አሻራ”
Next articleኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው መስኮች የጋራ ሥምምነት አካሄዱ።