
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከረጂሙ የኢትዮጵያ አነጋጋሪ እና ውጣ ውረድ የበዛበት ታሪክ ጋር ዘመናትን የተሻገረ ቁጭት አዘል ትውስታ አለው፡፡ በሀገሪቷ የዘመናት ኑባሬ ውስጥ የመሪነት እድል እና አሻራ የነበራቸው ነገስታት እና መሪዎች ሁሉ የተስፋ ዓይን አርፎበት አልፏል፡፡ ከውስጥም ከውጭም ኀይል እና እድል ያጋጠማቸው የሀገሪቷ ጥንተ ጠላቶች የፖለቲካ ልሳን መዘወሪያቸው አድርገውትም ቆይተዋል የዓባይ ወንዝን፡፡
ከኢትዮጵያ አብራክ መንጭቶ፤ ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን እና ግብጽን አቆራርጦ እስከ ሜዲትራኒያን የተዘረጋው የዓለማችን ሽንጠ ረጀሙ ወንዝ ዓባይ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ የገበረውም፤ የፈየደውም አንዳች አበርክቶ አልነበረውም፡፡ ቁጭታቸውን እና ብሶታቸውን በእንጉርጉሮ ሲያስተጋቡ የኖሩት ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት ቢያጡ ስም ያወጡበታል፤ ዜማ ያንቆረቁሩበታል፤ ልጥ ይነክሩበታል፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ዓባይ ለኢትዮጵያዊያን ከዚህ የዘለለ እና ውኃ የሚያነሳ አበርክቶ ግን አልነበረውም፡፡
ታሪክ በማስረጃ ከከተበው እውነት ብንነሳ እንኳን ዓባይን ገድቦ ለሀገሬው ልጆች ጸጋ ማዋል ሕልሙ ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያልፋል፡፡ ግብጽ በቋሚነት ከልካይ በኾነችበት ሚዛን የሳተ የዓባይ ውኃ ስሁት ትርክት ሸምጋይ የጠፋበት ዓለም አቀፍ አውድ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ እውን ነበር፡፡ ማርሽ ቀያሪ ትውልድ ተፈጥሮ ዓባይ በሀገሩ ማደር እና መዋል እስኪጀምር ድረስ ለቀሪው ዓለም ባለቤትነቱ እንኳን በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡
እንደ በኩር ልጅ ስሙ የበዛው ዓባይ “ናይል” የተሰኘ የባዕድ ስም ተሰጥቶት ብዙዎች እንዲስቱም፤ እንዲሳሳቱም ተደርገዋል፡፡ አንድ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ታሪካዊ ዳራን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ፕሮፌሰር ላውረንስ ፍሪማን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የምጣኔ ሃብት ብቻ ሳይኾን ፍትሐዊ የኾነ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም አብዮትንም አቀጣጥሏል ነበር ያሉት፡፡
የዓባይ ውኃ ውዝግብ ለሺህ ዘመናት የዘለቀ ቢኾንም ቅኝ ገዥዎች እግራቸው አህጉሪቷን ከረገጠበት ወቅት ጀምሮ ደግሞ የበለጠ የሴራ ማዕከል እንዲኾን ተደርጓል የሚሉት በርካታ ናቸው፡፡ ከተፋሰሱ ሀገራት በላይ ቅኝ ገዥዎች ለዘመናት እንዳሻቸው የዘወሩት የዓባይ ውኃ አሁንም ድረስ የውኃው ባለቤት ሀገራት ባይተዋር የኾኑበት ቀደምት ሥምምነቶች እንደማጣቀሻ ሲነሱ ይስተዋላል፡፡
በዓባይ ወንዝ የውኃ መጠን ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ በወንዙ ያላት ተጠቃሚነት እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ምንም የሚባል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ስሌት 2011 ላይ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ይፋ ስታደርግ ከተፋሰሱ ሀገራት በላይ ዓለም አቀፍ ጫናው እና ሙግቱ ብርቱ ኾኖ ብቅ አለ፡፡
በተለይም ባለፉት 13 ዓመታት በግልጽ እና ስውር መንገድ ካይሮ የምታስተባብረው የዓባይ ውኃ ሙግት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሰለባ ኾኖ ተስተዋለ፡፡ ነገር ግን ያንን ሁሉ ፈተና እና ውጣ ውረድ በትዕግስት፣ በጽናት እና በብስለት ያለፈችው ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ በተጀመረ በ13ኛ ዓመቱ 95 በመቶ የግድቡን ሥራ አጠናቅቃ የኀይል አቅርቦት ተጠቃሚ ኾነች፡፡
የግድቡ ግንባታ በተጀመረ በ13ኛው ዓመት እና የግድቡ ግንባታ 95 በመቶ በተጠናቀቀበት በዚህ ጊዜ እንኳን አሁንም ካይሮ መራሹ የአባይ ውኃ ውዝግብ አልተቋጨም፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ ቦስተን በታፍትስ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር፤ የፍሌቸር ሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት የሲቪል እና የአካባቢ ምህንድስና ፕሮፌሰር ሻፊቁል ኢስላም “ዓለም አቀፍ የውኃ ሥምምነቶች በተገቢው መንገድ አልተያዙም፤ የሚሻለው ትብብር እና በጎ ፈቃድ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ካለው ግርግር አንፃር የትብብር እና የንግግር በጎ አመለካከት እጅግ ጠቃሚ ጽንሰ ሃሳብ እንደኾነ ያነሳሉ።
ከውስጥም ከውጭም፤ ቀጣናዊውም አካባቢያዊውም፤ አሕጉራዊውም ዓለም አቀፋዊውም ተፅዕኖዎች እና ወከባዎች ባሉበት ኢትዮጵያ ግድቡን በተባበረ ክንድ ዳር አድርሳዋለች፡፡ “የማርሽ ቀያሪ ትውልድ ደማቅ አሻራም” ዘመን ተሻግሮ ተፅዕኖ ፈጥሮ የሚታይበት ጊዜ ሩቅ አይኾንም፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!