
ደሴ: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባቲ ከተማ “ቃልን በማክበር እግርን መትከል” በሚል መሪ መልእክት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከከተማዋ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሰላም የውይይት መድረክ አካሂዷል። እንደ ክልል የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት ሕዝቡን በማወያየት ክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦት በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በውይይት መድረኩ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉ እጅግ ከፍተኛ መጎሳቆል እንደደረሰበት የተነሳ ሲኾን ለተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ሁሉን ያሳተፈ ውይይት በማድረግ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተነግሯል። የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የኾነችው ባቲ ከተማ መሪዎች የጽንፈኝነትን ሃሳብ አምርሮ በመታገል ለውጥ ማምጣት ስለመቻሉ በጥንካሬ ተነስቷል። በቀጣይም ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ልማት መገባት እንዳለበት ተገልጿል።
እንደ ክልል የገጠመውን የሰላም እጦት ለመፍታት የሕግ ማስከበር ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ በማስቀጠል ነፃ ብቁ እና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት፤ የተሳሳተ ትርክትን በማረም የወል ትርክቶችን በመገንባት ሰላምን ለማጽናት ሁሉም አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መስማማት ላይ ተደርሷል።
በውይይት መድረኩ የተካፈሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለገጠመው የሰላም ችግር መሰል የምክክር መድረኮች አስፈላጊ መኾናቸውን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ መንግሥት ጎን እንደሚሰለፉም ተናግረዋል። “ክልሉም ኾነ ዞኑ የፀጥታ ችግር ውስጥ ቢኾንም በባቲ ከተማ አመራሩ በቅንጅት በሠራው ሥራ አንፃራዊ ሰላም በማምጣት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ሳይቋረጡ ቀጥለዋል” ያሉት የባቲ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሰይድ መሐመድ ናቸው።
“ክልሉ የሰላም እጦት ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ተደጋጋሚ ሕዝባዊ የሰላም ውይይቶች መደረጋቸውን በማውሳት ኀብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር እንደክልል ከገባንበት የሰላም እጦት በጋራ ልንወጣ ይገባል” ሲሉ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እብሬ ከበደ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!