
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልእክት የገቢ አሠባሠብ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። የገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ በ2016 በጀት ዓመት መግቢያ ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሠባሠብ ሥራው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በታማኝ ግብር ከፋዮች እና በሕዝቡ ርብርብ የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው “ሰላም ለገቢ አሠባሠባችን እንደ እስትንፋስ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ መኖር አለበት፤ ይህ ሲኾን የተሻለ ገቢ መሠብሠብ ይቻላል ነው ያሉት። በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ መሠብሠቡን ገልጸዋል።
ይህ አፈጻጸም ከገጠመው የጸጥታ ችግር አኳያ ሲታይ በታማኝ ግብር ከፋዮች፣ በቢሮው ታታሪ ባለሙያዎች እና በልማት ወዳዱ ሕዝብ ርብርብ የመጣ ውጤት ነው ብለዋል። የተሠበሠበው ገቢ ከእቅዱ አኳያ ሲታይ አናሳ በመኾኑ ተጨማሪ ርብርብ እንደሚፈልግም አሳስበዋል።
ቢሮ ኀላፊው የከፋ የሰላም ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች የገቢ አሠባሠብ ሥራው ዝቅተኛ እንደነበር ጠቅሰው አንጻራዊ ሰላም የነበረባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበራቸው ጠቁመዋል።
በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነውም የገቢ አሠባሠብ እቅዳቸውን በበቂ ሁኔታ የፈጸሙ ባለመልካም ተሞክሮ ዞን እና ወረዳዎች እንዳሉም ጠቁመዋል። ለአብነትም ከሰሜን ወሎ ዞን የመርሳ እና ከሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ጥሩ የእቅድ አፈጻጸም በማስመዝገብ ልዩ እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ወረዳዎች ኾነዋል።
አቶ ክብረት ቢሮው የተሻለ አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት እና የተሻለ የግብር መሠብሠቢያ ቴክኖሎጅ በመዘርጋት ተመጣጣኝ ገቢ ለማግኘት እንደሚሠራም ገልጸዋል። የታክስ አሥተዳደሩ ከኃላ ቀርነት ወጥቶ ዘመናዊ እና የተቀላጠፈ መኾን እንዳለበትም ገልጸዋል።
በቂ ገቢ ሠብሥቦ መገኘት ሕዝባችን የናፈቀውን ልማት እውን ለማድረግ እና በችግር ውስጥ ያሉትን ወገኖችም በራስ አቅም ፈጥኖ ለመርዳት ያግዛል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው። ስለዚህ ሁሉም ዜጎች “ግብር ዞሮ ለራስ እና ለሕዝብ” መኾኑን በመገንዘብ የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!