“ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድህነትን በራስ አቅም ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን የፈነጠቀ የክፍለ ዘመኑ ስኬት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

58

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መጋቢት 24 የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጅማሮ የታወጀበት 13ኛ ዓመት እና የለውጡ መንግሥት 6ኛ ዓመት ምስረታ የሚታሰብበት ዕለት መኾኑን አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር ፋና ወጊ ትልም ጅማሮ “ሀ” ብሎ የተጠነሰሰበት ጊዜ መጋቢት 24 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፋይዳ እና ተምሳሌትነቱ ተፈጥሯዊ የወንዝ ውኃ ፍሰትን ለኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የማዋል ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ሃብት እያላት በድህነት አረንቋ ውስጥ ለምትማቅቀው አህጉራችን አፍሪካ ድህነትን በራስ አቅም ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን የፈነጠቀ የክፍለ ዘመኑ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

ግድቡ ለኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል የአፍሪካውያንን ነፃ መውጣት በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትግላችው አባቶች ትምህርት እንደሰጡ ሁሉ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ደግሞ የአባቶች ልጆች ድህነትን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ታግለን ማሸነፍ እንደምንችል ዳግም ትምህርት የሰጠንበት በመኾኑ ኮርተናል ነው ያሉት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የለውጡ መንግሥት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የገጠሙትን ችግሮች ፈጥኖ በማረም እና ግንባታው በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲከወን፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ እየተመራች ላስመዘገበችው ዕድገት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነታችንን እያጠናከርን “ብሔራዊነትን” በማጎልበት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ሁሌም እንተጋለን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት። ያሉብንን ሀገራዊ ችግሮች በአጠረ ጊዜ ውስጥ በመፍታት የብልፅግና ጉዟችንን እናፋጥለንመ ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ መኾናቸውን በአዳርቃይ ወረዳ የዛሬማ ንዑስ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
Next article“ሰላም ለገቢ አሠባሠባችን እስትንፋስ ነው” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ