ቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ መኾናቸውን በአዳርቃይ ወረዳ የዛሬማ ንዑስ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

56

ደባርቅ: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዳርቃይ ወረዳ ቆላማ የአየር ንብረት ያለበት እና ለቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ ምቹ የኾነ የሰሜን ጎንደር ዞን ወረዳ ነው። በወረዳው ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ አምስት ትላልቅ ወንዞች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ በዛሪማ ንዑስ ወረዳ የሚገኘው የዛሪማ ወንዝ ተጠቃሽ ነው። የአካባቢው አርሶ አደሮችም ወንዙን ተጠቅመው ቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ተጠቃሚ እየኾኑ ነው።

አቶ መልካሙ ኪዴ በአካባቢው በቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደር ናቸው። አርሶ አደሩ ውኃ ገብ መሬቱ እና አትክልቱም እያላቸው ጠቀሜታውን በውል ሳይረዱት ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱም ማሳቸውን አልምተው መጠቀም እንደሚችሉ ግንዛቤ በማግኘታቸው ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ልማቱ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በማሳቸው ሙዝ እና ማንጎ በሰፊው በማልማት በቅርቡም ፓፓያን በመጨመር በዓመት ከ300 ሺህ ብር ያላነሰ ገቢ እንዳገኙ ተናግረዋል። ከልማቱ በሚያገኙት ገቢም ልጅ ማሳደግ እና ማስተማር፣ ቋሚ ንብረት ማፍራትም ችለዋል።
በወንዝ ዳርቻ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች ወደ ልማቱ ገብተው ተጠቃሚ እንዲኾኑም አርሶ አደሩ መክረዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አቶ ግርማይ ጀጃው በተመሳሳይ የዛሪማ ወንዝን ተጠቅመው የተለያዩ ቋሚ አትክልቶችን እያለሙ ነው። ቋሚ አትክልቶቹ ለፍሬ ሲደርሱ ለምግብ ከመጠቀም ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነግረውናል። ቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ አንዴ ከተተከለ በየዓመቱ ገቢ የሚያስገኝ በመኾኑ ተመራጭ ልማት መኾኑንም አስረድተዋል።

የአዳርቃይ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሹምዬ ነጋሽ በወረዳው በቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ለረጅም ዓመታት እያለሙ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች መኖራቸውን አስታውቀዋል። በወረዳው ዓመቱን ሙሉ በሚፈስሱት ወንዞች ዳርቻ ማሳ ያላቸው ኹሉም አርሶ አደሮች ከመኸር ሰብል ልማት በተጨማሪ ማሳቸውን በቋሚ አትክልት እንዲሸፍኑ እና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ እቅዳችን ነው ብለዋል። ይህን ለማሳካትም ለአርሶ አደሮች ሥልጠና እና ምርጥ ዘር በመስጠት እያገዙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

የማንጎ ተክል ኋይትስኬል በተሰኘ በሽታ ችግር እየገጠመው በመኾኑ በፓፓያ፣ ሙዝና ቡና ተክሎች ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሹምዬ ለዚህም በሦስት ጣቢያዎች ችግኝ የማፍላት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሐንስ ይግዛው በዞኑ ደጋማ የኾኑ አካባቢዎች ለአፕል ተክል፣ ቆላማ የኾኑት ደግሞ ለሙዝ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና መሰል ተክሎች ተስማሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ደጋማ በኾኑ አራት ወረዳዎች በ11 የችግኝ ጣቢያዎች 21 ሺህ አፕል እና መሰል የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላት ላይ መኾናቸውን አመላክተዋል። ምዕራብ ጠለምት ላይ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ሙዝ በሰፊው እየለማ እንደሚገኝ ያነሱት ምክትል ኀላፊው ልምዱን ወደ አዳርቃይ እና ሌሎች አካባቢዎች በመውሰድ አርሶ አደሩ የበለጠ ተጠቃሚ የሚኾንበትን መንገድ እያመቻቹ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት። በ14 ችግኝ ጣቢያዎች ከ88 ሺህ በላይ የቆላ ፍራፍሬ እየተፈላ ይገኛል። ችግኞችን የመከተብ ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል። ዞኑ ለልማቱ ካለው ምቹ ሁኔታ አንጻርም በተሻለ ደረጃ በማሳደግ እና በሳይንሳዊ መንገድ በመደገፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በውጭ ብድር እና እርዳታ ላይ የተመሰረተች ሀገር የተሻለ ሉዓላዊነት ሊኖራት አይችልም” የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋየ ቱሉ
Next article“ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድህነትን በራስ አቅም ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን የፈነጠቀ የክፍለ ዘመኑ ስኬት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ