
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልእክት ክልል አቀፍ የገቢ አሠባሠብ ንቅናቄ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋየ ቱሉ የሀገሪቱ የታክስ ሥርዓት ረጅም እድሜ ያለው ቢኾንም አሁን የሚሠበሠበው የገቢ መጠን ከልማት ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ እንዲኾን ግን ጠንካራ ሥራን ይፈልጋል ብለዋል።
አማራ ክልል የተሻለ ገቢ ከሚሠበሥቡ ክልሎች ውስጥ አንዱ መኾኑንም ገልጸዋል። ክልሉ የሰላም ችግር ቢገጥመውም ገቢ የሀገር እና የሕዝብ ሕልውና መኾኑን በመረዳት ተገቢውን ገቢ ለመሠብሠብ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል። የገቢ አሠባሠብን ለማሳደግ በተለይ የታክስ አሥተዳደርን በቴክኖሎጅ የማዘመን ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ይህንንም ከክልሎች ጋር በመነጋገር ተጠናክሮ ይሠራል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው። የተጀመሩ ቴክኖሎጂዎች ሲተገበሩ ከደረሰኝ ጋር የተያያዙ እና መሰል ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የክልሎች የጋራ ገቢ የተሻለ እድገት እያሳየ ነው፤ አማራ ክልልም ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ያለበት በመኾኑ በልማት ፍላጎት ልክ የኾነ ገቢ ለመሠብሠብ ትልቅ እድል ያለበት ነው ብለዋል። በገቢ አሠባሠብ ሥርዓት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት የገቢ መጠንን ከፍ ለማድረግ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
“በውጭ ብድር እና እርዳታ ላይ የተመሰረተች ሀገር የተሻለ ሉዓላዊነት ሊኖራት አይችልም” ሲሉም ተናግረዋል። በመኾኑም ከእዳ እና ከብድር ከሚገኝ ገንዘብ ይልቅ ከግብር እና ታክስ ከሚገኝ ገንዘብ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ጠንካራ እና የልማት ጥያቄን የሚመጥን ገቢ መሠብሠብ የተሻለ ዲሞክራሲ፣ ሰላም እና ልማት ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው ሲሉም ተናግረዋል ሚኒስትር ደኤታው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!