
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ መልእክት ምስጉን ግብር ከፋዮችን፣ ታታሪ ሠራተኞችን እና አጋር አካላትን ለማበረታታት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስትር የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ግብራቸውን በታማኝነት በመክፈል ለክልሉ ከፍቸኛ ገቢ ያስገኙ ግለሰቦች እና ተቋማት ምሥጋና፣ እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ከሸለሙ በኃላ የመድረኩን የመዝጊያ ንግግር በማድረግ የሥራ መመሪያም አስተላልፈዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አማራ ክልል በርካታ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የሚነሳበት ክልል ነው፤ ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ተመጣጣኝ ገቢ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። በክልሉ ከሚመረተው ምርት እና ካለው የኢኮኖሚ አቅም አኳያ የሚሠበሠበው ገቢ አናሳ መኾኑንም አመላክተዋል። ክልሉ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ቢኾንም ግብር በመክፈል ረገድ ግን ውስንነቶች አሉ ነው ያሉት።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ታታሪ ሠራተኞችን በማፍራት ለክልሉ ልማት እና ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጅ ገቢ ለመሠብሠብ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ገቢ አሠባሠቡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና የተቀላጠፈ እንዲኾን የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ “ከድሃ ሕዝብ ላይ ግብር በመሰወር ሃብት አንነጥቅም ያላችሁ ታማኝ ግብር ከፋዮች ክብር ይገባችኋል” ሲሉም ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ግለሰቦች እና ተቋማትን አመሥግነዋል። ለሕዝብ ልማት በማሰብ ግብራቸውን በታማኝነት የሚከፍሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ቢኖሩም ሕዝብ እና ሀገርን ረስተው ለራሳቸው ብቻ ሃብት ለማጋበስ ግብር የሚሰውሩም እንዳሉ አመላክተው፤ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል። ታማኝ እና ለሕዝብ ልማት የሚያስቡ ግብር ከፋዮች ሁልጊዜም ከክልሉ ሕዝብ ጎን በመቆም መሠረታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ክልሉ በእርዳታ እና በብድር ልማት መሥራት የለበትም፤ ስለዚህ ጠንካራ የገቢ አሠባሠብ ሥርዓት በመዘርጋት የልማት ጥያቄን የሚመልስ ገቢ ለመሠብሠብ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ግብር የመጨረሻ ግቡ የሕዝብን ልማት መሥራት መኾኑን በመገንዘብ ከአርሶ አደሮች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ነጋዴዎች እና ተቋማት ድረስ ጠንካራ የኾነ ግብር የመክፈል ባሕል ሊዳብር እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!