
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብርቱ እጆች ወራጅ ውኃን ይገራሉ፣ አስፈሪ ማዕብልን ያስታግሳሉ፣ ተጓዡን ያሳርፋሉ፣ ብርቱ ልጆች ነገን ይተነብያሉ፣ ዛሬ ላይ ኾነው ስለነገ እና ከነገ ወዲያ ለሚሆነው ዘመን ይሠራሉ፣ ዘመናቸውን ያሳምራሉ፡፡ የልጅ ልጆቻቸውን እጣ ፈንታ ብሩህ ያደርጋሉ፡፡
ብርቱ እጆች ተፈጥሮን ያስጌጣሉ፣ በላባቸው እና በደማቸው የከበረ ታሪክን ይጽፋሉ፣ ዘመናት አልፈው ዘመናት በተተኩ ቁጥር የማይናወጥ የታሪክ ሐውልት ያቆማሉ፤ ለታላቅነታቸው ሕያው አሻራ ያኖራሉ፡፡ ብርቱ እጆች ተባብረው ይሠራሉ፣ የሚገፋቸውን ይጠላሉ፣ የሚተናኮላቸውን ይቀጣሉ፤ የስልጣኔን ጎዳና ያሳምራሉ፤ ለልጅ ልጆቻው ያማረ ጎዳና ያለሰልሳሉ፤ በጎዳናው ጫፍም መልካሙን ነገር ያስቀምጣሉ፡፡
አንድነት ታሪክ ይሠራል፤ አንድነት ትውልድ ያኮራል፤ አንድነት ሀገር ይጠብቃል፤ አንድነት ሉዓላዊነትን ያስከብራል፤ አንድነት ነጻነትን ያጸናል፤ ከእነ ክብር እና ከእነ ኩራት ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነታቸው እንደ ዓለት የጠጠረ ነጻነት አኖረዋል፤ በእሳት የታጠረች ሀገር አቆይተዋል፤ በታሪክ የከበረች ምድር ለልጅ ልጅ አስረክበዋል፤ ታሪክ በደማቅ ቀለም የጻፈው አሻራ ከትበዋል፤ በአንድነት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ደርሰዋል፤ የጭንቅ ቀን ደራሾች፣ የመከራ ቀን አበጋዞች፣ የጨለማ ዘመን ማያ መብራቶች፣ የመከራ ማዕበል መሻገሪያዎች ኾነዋል፡፡
በረዘሙ ዘመናት የሠሯቸው አኩሪ ታሪኮቻቸው ሁሉ የአንድነት ውጤቶች ናቸው፡፡ አንድ ኾነው የሠሯቸው፣ አንድ ኾነው ያበጇቸው፣ አንድ ኾነው ያስጌጧቸው፡፡ እነሆ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን በአንድነት የረቀቀ አሻራ አስፍረዋል፡፡ የከበረ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ስለ ምን ቢሉ አንድነት ጠፋ በተባለበት፣ የኢትዮጵያውያን የኖረ ብርታት ሟሸሸ እየተባለ በሚታማበት ዘመን አንድነታቸውን አጠናክረው፣ የቆዬውን መንፈስ ተላብሰው፣ ለዘመናት የፈሰሰን ወንዝ ገድበዋል፤ የእድገታቸውን መሠረት ጥለዋልና፡፡ ዓባይ የአንድነት ውጤት፣ የዘመን መብራት ነው፡፡
አንድ የኾኑ እጆች አስውበው የሠሩት፤ ዘመን የሚገለጥበት አድርገው ያረቀቁት፣ ዓባይ የኢትዮጵያውያን ተስፋ ነው። ዓባይ የኢትዮጵያ ኩራት ነው፣ ዓባይ የኢትዮጵያ ሌላኛው ጌጥ ነው፣ ዓባይ አንድነት የሚሰበክበት ሐውልት ነው፣ ዓባይ መተሳሰብ የሚነገርበት የፍቅር ማዕድ ነው፣ ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ከወንዝነት የተሻገረ፣ ከግድብ ያለፈ ሕያው ምልክት ነው፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርሰቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፍልስፍና መምህር አወል አሊ የዓባይ ግድብ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለታላቅ ዓላማ የቆመ፣ ለሀገር መልክት የሚኾን፣ የሕዝብ አንድነት፣ ኅብረት ውጤት ነው ይሉታል፡፡ ዓባይ በብዙ ፈተናዎች መካከል ዛሬ ላይ የደረሰ፣ ወደ መጠናቀቁም የቀረበ ነው፡፡ ዓባይ ለሀገር እድገት ታላቅ መሠረት የሚጥል ታላቅ ግድብ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ዓባይ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ ይመጣል፤ ለኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ይፈጥራል፤ ግድቡ ገና በግንባታ ላይ እያለ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥሯል፤ ሲጠናቀቅ ደግሞ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ይፈጥራል፤ ዓባይ ሰው ፈላጊ ነው፤ ለከተሞች መስፋፋት እድል የሚፈጥር ነው፡፡ በዓባይ ምክንያት ታላላቅ ከተሞች ይመሠረታሉ፣ ከተሞች ሲመጡ ዘመናዊ አኗኗር ይጀመራል፤ የፈጠራ ሥራዎች፣ ፋብሪካዎች ይሠፋሉ፣ ሀገርም ታደለች አሉን፡፡
ዓባይ ዘመናዊ ግብርናን ያመጣል፤ የመስኖ አቅርቦት ይኖረዋል፤ በግብርናው ዘርፍ ታላቅ እድል ይዞ ይመጣል፤ ራስን ያስችላል፤ ቆይቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ያስመርታል፤ ዓባይ ሐይቆችን የሚፈጥር ግድብ ነው፣ ይህም ሲሆን ዘመናዊ የዓሳ እርብታ ይኖራል፤ የዓሳው እርባታም ከራስ አልፎ ለሌሎች ገበያ የሚቀርብ ይኾናል ነው የሚሉት፡፡ በርካታ ሀገራት ምጣኔ ሀብታቸውን የቀየሩት በዓሳ ምርት ነውና፡፡
ዓባይ ለዘመናት በጭስ ለተደበቁ ደጋግ ኢትዮጵያውን እናቶች ብርሃን ይዞ ወደ ጓዳቸው የሚገባ ተስፋ ነው፡፡ ዓባይ ከጭስ የሚያላቅቃቸው፣ የኩራዝ ምትክ ነው፡፡ ዓባይ ነዳጅን የሚተካ ኀይል ይዞ የሚመጣ ብዙ እጆች የገነቡት፣ ብዙ ተስፋዎች እና ብዙ ጥቅሞች ያሉት ግድብ ነው፡፡ ታላቁ ግድብ በዓባይ (ናይል) ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ይቀይረዋል ይሉታል መምህሩ፡፡ በግብጽ ነጋሪነት እና በሌሎች ሀገራት ተከታይነት ሲዘወር የኖረውን የናይል ፖለቲካን አሰላለፍ ዓባይ አካሄዱንም፣ ሀሳቡንም፣ መድረሻውንም ይቀይረዋል፤ የዓባይ (ናይል) ፖለቲካ በውጥረት ውስጥ ያለ ፖለቲካ ነው፣ ከላይኛው እና ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል እንጠቀማለን፣ አትጠቀሙም፣ እንሠራለን አትሠሩም የሚባሉ እሰጣገባዎች መልተውበታል፤ ግፊቶች እና መጓተቶች አሉ፡፡ የሕዳሴ ግድ ግን ይሄን መጓተት ይቀይረዋል እንደ አቶ አወል ገለጻ፡፡
እንዴት ኾኖ ቢሉ ኢትዮጵያ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምታገኘውን ኀይል ለራሷ ተጠቅማ የተረፋትን ኀይል ለጎረቤት ሀገራት የምትሠጥ ከኾነ በጎረቤት ሀገራት እና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ የኾነ መተሳሰር ይፈጠራል፤ አንደኛው በሌላኛው ላይ ተስፋ የሚደራረግበት፣ የጋራ የኾነ እጣፈንታ ላይ የተመሠረተ ሕዝበ ይፈጥራል፡፡
ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኃይል የሚያገኙ ከኾነ ድጋፋቸውን ለኢትዮጵያ ያደርጋሉ፣ ኢትዮጵያ የበላይነቷን እንድታስጠብቅ እና የመጠቀም እድሏ ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉም ሃሳባቸውን አክለዋል። የዓባይ ግድብ ከግድብ በላይ የኾነ ታላቅ ፕሮጄክት ነውም ይሉታል መምህሩ፡፡ የኤልክትሪክ ኀይልን ለሀገራት በመስጠት የውጭ ምንዛሬን የምታገኝበት፣ የምሥራቅ አፍሪካን፣ የዓባይ ፖለቲካን የሚቀይር፣ የኢትዮጵያን አጋር የሚያበዛ ነው ይላሉ፡፡ ዓባይ የዲፕሎማሲ ማሳመሪያም ነው፤ ኢትዮጵያን የሚሞግቱ የነበሩ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጥቅም የሚያገኙ ከኾነ እጣ ፈንታቸው ከሕዳሴ ግድቡ ላይ ይኾናል፤ በግድቡ ከመሞገት ይልቅ ግድቡን ወደ መጠበቅ ይሻገራሉ፣ ከፉክክር ይልቅ ወደ ጋራ ትብብር ይሄዳሉ።
ኢትዮጵያ ኀይልን ለውጭ ገበያ የምታቀርብ ከኾነ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በደኅንነት አያሌ ጠቀሜታዎችን ይዞላት ይመጣል፤ ኢትዮጵያን ከሚያሰጓት ሀገራት ይልቅ የሚጠብቋት ይበዛሉ፤ ጎረቤት ሀገራትን የራሷ ጠባቂዎች እና አጃቢዎች ማድረግ ያስችላታል ብለዋል ምሁሩ፡፡
የሕዳሴ ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለውን አዋጥቶበታል፤ ግድቡን ለመጠበቅ ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ከየትኛውም ብሔር ጋር ማያያዝ አስፈላጊ አይደለም፤ ግድቡ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ብቻ ነው ብሎ ማመን ያስፈልጋል፤ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት እና የአንድነት ተምሳሌት ነው፣ ዓባይን የሀገር አርማ ነው ብሎ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መጣ ሄደ፣ የትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ኖረ አልኖረ፣ የትኛውም ግለሰባዊ እይታ ኖረ አልኖረ፣ ግድቡ ሁልጊዜ የሚኖር፣ ከኢትዮጵያ እና ከባንዲራው ጥቅም ጋር አብሮ የሚሰለፍ ነው ብሎ ማሳብ ይገባል ነው ያሉት መምህሩ፡፡
ግድቡን ከሀገር ጥቅም፣ ሉዓላዊነት፣ ከሀገር ምልክትነት፣ ከጋራ ሀብትነት ጋር አጣምሮ መያዝ፣ ግድቡን ለመጠበቅ የሚኖርን ወኔ፣ ቁርጠኝነት ከፍ ያደርጋል፤ ግድቡን መጠበቅ ሀገርን፣ የሀገርን ክብር፣ ሉዓላዊነት መጠበቅ ነው ይላሉ፡፡ ግድቡን የኾነ አካል መጥቶ እነካለሁ ቢል ፈጽሞ የማይነካ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነገር ቢያለያየንም፣ በግጭት እና በውጣ ውረድ ውስጥ ብንኖርም ብሔራዊ ምልክት በኾነ ግድብ ላይ ግን አንድ መኾናቸውን የምናሳይበት ታላቅ ምልክት ነው ይሉታል፡፡
ይህ አይነት እምነት እና አመለካከት ካለ ግድቡን በክፉ የሚሞክረው የለም፣ ዓለም አቀፍ ተጽዕኗችንም ከፍ ይላል ነው ያሉት፡፡ ዓባይ ከግድብ ያለፈ ነው፡፡ ዓባይ የበዙ ተስፋዎችን እና እድሎችን ለኢትዮጵያ ይዞ የሚመጣ እንደ ስሙ ሁሉ ታላቅ ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!