“ኦቪድ ገላን ጎራ” የተባለ አዲስ የከተማ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

96

አዲስ አበባ: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 60 ሺህ ቤቶች ይገነቡበታል የተባለው አዲሱ ከተማ ፕሮጀክት የሚገነባው በደቡባዊው የአዲስ አበባ ክፍል አቃቂ ቃሊቲ ወይም ቦሌ ቡልቡላ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አለፍ ብሎ ነው። በግል እና መንግሥት አጋርነት በ70/30 መርህ የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ ከተማ አሥተዳደሩ በያዘው አቅጣጫ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከኦቪድ ግሩፕ ጋር በመኾን በኦቪድ ሪል ስቴት አማካኝነት የሚገነባ ፕሮጀክት ይኾናል።

558 ሺህ በላይ ሄክታር የሚሸፍን ሰባተኛው ትልቅ ከተማ ኾኖ የሚገነባው ይህ የኦቪድ ገላን ጉራ ከተማ ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን አሟልቶ ይገነባል ነው የተባለው። አዲሱ ከተማ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሏል። ፕሮጀክቱ 300 ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚኾንበት ሲኾን የመኖሪያ፣ የመዝናኛ እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት የሚኖሩት ዘመናዊ ከተማ እንደኾነም ተገልጿል።

ቤቶቹ ስታንዳርድ፣ ዴሉክስ እና ፕሪሚየም የተባሉ በሦስት ደረጃዎች የተከፈሉ ቤቶች ናቸው። የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ዮናስ ታደሠ ፕሮጀክቱ የቤት ግንባታ ብቻ ሳይኾን ዘመናዊ ከተማ ነው ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ተነሺ አርሶ አደሮች ቤት የሚሰጣቸው ይኾናል ብለዋል። ፕሮጀክቱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ኢንጅነር ዮናስ ከተማውን በሕክምናው ዘርፍ የሜዲካል ከተማ የማድረግ እቅድም መኖሩን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ክንቲባ አዳነች አቤቤ “ላለፉት ስድስት ዓመታት ቃል የገባነውን የፈጸምንበት እና የምንፈጽምበት ቀን ነው” ብለዋል። “በርካታ ሰው ተኮር ሥራዎች እና ከተማዋን እንደስሟ አድርገን እንገነባለን ያልነውን በተግባር ያሳየንባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ዕውን ማድረግ ችለናል” ነው ያሉት ከንቲባዋ።

ከተማ አሥተዳደራቸው ከ200 ሺህ በላይ ቤቶችን በስድስት ዓመት ውስጥ መገንባት መቻሉንም ከንቲባዋ ተናግረዋል። አሁንም በበቂ ሁኔታ ማሟላት ያልተቻለውን የቤት ልማት መንግሥት ብቻውን ሊያሳካ አይችልም ብለዋል።ስለኾነም ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ መሥራት አስፈላጊ በመኾኑ ሌሎችም የኦቪድ ግሩፕን አርዓያ ተከትለው አብረው እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ በመኾኑ ድጋፉን እንዲያሳይ ጠይቀዋል። ከ200 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ፕሮጀክት መኾኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልቃድር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ እንዲሁም የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዮናስ ታደሠ በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግድቡ እንደ ላሊበላ፣ አክሱም እና ፋሲል የሀገር ኩራት የሚኾን ሃብት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ዓባይ የአንድነት ውጤት፤ የዘመን መብራት”