“ግድቡ እንደ ላሊበላ፣ አክሱም እና ፋሲል የሀገር ኩራት የሚኾን ሃብት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

59

አዲስ አበባ: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀው የህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት በዓል በፓናል ውይይት እና በፎቶ አውደ ርዕይ እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉ “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ መልእክት ነው በአዲስ አበባ እየተከበረ የሚገኘው፡፡

በበዓሉ ላይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የህዳሴ ግድቡ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል። የበዓሉ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን የፎቶ አውደ ርዕይ ከፍተዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር ብትኾንም ሃብቶቿን በተገቢው ልክ እየተጠቀመች አለመኾኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡ “የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ኩራታችን የሚኾን ሃብት ነው” ብለዋል።

“ግድቡ እንደ ላሊበላ፣ አክሱም እና ፋሲል የሀገር ኩራት የሚኾን ሃብት ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባታው ሥራ ሳይቋረጥ እዚህ የመድረሱ ሚስጥር የኅብረት ሥራው ተጠናክሮ በመቀጠሉ እንደኾነ አስረድተዋል።

ግድቡን 95 በመቶ ማጠናቀቅ የተቻለው በትብብር፣ በራስ ሃብት እና ትጋት መሥራት በመቻሉ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይም የግንባታ አጀማመሩ ላይ የነበረውን የአንድነት ትብብር በማጠናከር የግድቡን ፍጻሜ ማፋጠን ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢ አሠባሰብ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።
Next article“ኦቪድ ገላን ጎራ” የተባለ አዲስ የከተማ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።