የህዳሴ ግድብ ሀገራዊ ሃብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ገለጹ።

27

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሠረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም ሀገራዊ ሃብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ገልጸዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ መልእክት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ አደረጃጀት አመራሮች እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለህዳሴ ግድቡ አስተዋጽኦ ያደረጉ የዲያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል። በበዓሉ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ባስተላለፉት መልእክት የህዳሴ ግድብ ሁሉም ዜጋ ሃብቱን፣ ዕወቀቱን እና ጊዜውን በማስተባበር የሚገነባው ልዩ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ግንባታው የሀገርን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግ ብሎም ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሠረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግ እና ሀገራዊ ሃብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር እንደኾነም አስረድተዋል። ከፕሮጀክቱ ጅማሮ አንስተው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የዲያስፖራ አባላት ምሥጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር ስለሺ በቀለ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ተሳትፎው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በዕለቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሠባሠቢያ ፕሮግራም መካሄዱን በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቁጥር ትንሽ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማኅበራትን መፍጠር ላይ ትኩረት ይደረጋል” የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን
Next articleየአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገቢ አሠባሰብ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።