“በቁጥር ትንሽ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማኅበራትን መፍጠር ላይ ትኩረት ይደረጋል” የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን

34

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በሕግ ማዕቀፍ ተደራጅተው ወደ ሥራ እንደገቡ ይነገራል። ከተመሠረቱ ከስድስት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ማኅበራት አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 110 ሺህ 584 መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 403 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኔኖች እና አምስት ክልላዊ ፌዴሬሽኖች መድረሳቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሺህሰማ ገብረሥላሴ ገልጸዋል።

በእነዚህ ማኅበራት 28 ሚሊዮን 582 ሺህ 5 አባል አላቸው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 9 ሚሊዮን 683 ሺህ 234 ሴቶች ናቸው። 59 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና 39 ሚሊዮን ብር ቁጠባ ከአባላት ማሠባሠብ መቻላቸውንም አንስተዋል። የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ በየዓመቱ በአማካይ 15 ሚሊዮን ብር ብድር እንደሚያቀርቡ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙት 110 ሺህ ማኅበራት ውስጥ 30 በመቶ የሚኾኑት በአማራ ክልል እንደሚገኙ አንስተዋል። ክልሉ በማኅበራት ቁጥር ከሀገሪቱ እንደኛ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በካፒታል አቅማቸው፣ በገበያ ተሳትፏቸው እና በቁጠባ እና ብድር አቅርቦት ሽፋናቸው ግን የቁጥሩን ያህል አለመኾኑን ገልጸዋል።

ማኅበራት ከተቋቋሙ ጀምሮ በግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ በግብይት፣ በከተሞች የኑሮ ውድነትን መፍታት፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤት ችግርን በመቅረፍ ላይ ትኩረት አድርገው ሲሠሩ ቆይተዋል። የቁጠባ ባሕልን በማሳደግ እና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ እንዲኹም የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ እና በመሳሰሉ ተግባራት ላይም ትኩረት አድርገው ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በቀጣይ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት በራስ አቅም የዳበረ ምጣኔ ሃብት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሥርዓትን እንዲገነቡ ይጠበቃል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ችግሮችን ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ የመለየት ሥራ ተሠርቷል። የአደረጃጀት፣ የአመራር እና የአሠራር ብቃት ጉድለት፣ የፋይናንስ አቅም እና አሥተዳደር ክህሎት ማነስ፣ ራስን ከሁኔታ ጋር ማጣጣም አለመቻል፣ የተወዳዳሪነት ችግር፣ ግልጽ የኾነ የፖሊሲ አቅጣጫ እና የሕግ ማዕቀፍ ችግሮች መኖራቸውም ተረጋግጧል። ይህን መሠረት ተደርጎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሪፎርም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የሪፎርሙን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ደግሞ ሪፎርሙን የመምራት፣ ምቹ ኢንቨስትመንት እና የንግድ አካባቢ የመፍጠር እና ድጋፍ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቅበቃል። ማኅበራት ደግሞ የሪፎርሙ ባለቤት መኾን፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በመለየት በደረጃ ለመፍታት መዘጋጀት፣ ከአባላት ጋር መተማመንን መፍጠር፣ ከአባላት በተጨማሪ ሃብት ማሠባሠብ፣ ተወዳዳሪ መኾን እና የአባላቱን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተሳትፎን ድርሻን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። በአጠቃላይ በቁጥር ትንሽ በተጽዕኖ ብዙ ማኅበራትን የመፍጠር አቅጣጫም ተቀምጧል። ክልሉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ኮሚሽኑ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዓላት ለኢትዮጵያውያን አብሮነትን፣ መቻቻል እና መተሳሰብን ለማጠንከርም ገመዶች ናቸው” ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ
Next articleየህዳሴ ግድብ ሀገራዊ ሃብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር) ገለጹ።