
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር አዲስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከፍተኛ መሪዎች፣ ምሁራን እንዲሁም አርቲስቶች ተገኝተው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ እንደገለጹት በዓላት ትውልድ የሚታነጽባቸው ከመኾናቸው ባለፈ የአንድ ሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል፡፡
በዓላት ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን መስተጋብር፣ አብሮነት፣ መቻቻል እና መተሳሰብን ለማጠንከርም ገመዶች ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህ በዓላት ያላቸውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባትም ከዚህ ቀደም በአዋጅ ቁጥር 16/1967፣ 28/1968 እንዲሁም 29/1988 የመነሻ አዋጅ ወጥቶላቸው ተግባራዊ ሲሆን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ አዋጆች የበዓላት አከባበር እና የሥራ ሰዓትን የሚመለከት መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የአሁኑ ረቂቅ አዋጅ የበዓላት ጉዳይ እና የበዓላት አከባበር ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የቀድሞውን አዋጅ የማሻሻል ሳይኾን በአዲስ አዋጅ መቀየር ላይ ያለመ መኾኑን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!