
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ አሥተዳደር ባለፉት ስምንት ወራት በተሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲሁም ባጋጠሙ የሰላም ችግሮ ላይ ከነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል። በክፍለ ከተማው የተከናወኑ ሥራዎች እና ያጋጠሙ ችግሮች ለውይይት ቀርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በኑሮ ውድነት፣ እና በሰላም ዙሪያ የመፍትሔ ሃሳቦችን አቅርበዋል።
የሰላም በር ቀበሌ ነዋሪው አቶ በላይ አሰሙ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል እና ግጭቱም በሰላም ተፈትቶ ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር መሠራት አለበት ብለዋል። በግጭቱ ሞት፣ ሠርቶ ለማደር መቸገር እና የኑሮ ውድነት ተባብሷል ያሉት አቶ በላይ ለሰላም መደፍረሱ ምክንያት የሚኾኑት አገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በትኩረት መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የደብረ ማርያም ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ወርቅነሽ ቸኮል በበኩላቸው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ስለማያመጣ ምክክሩ ትኩረት እንዲሰጠው፤ የሁሉም አካል ሰላማዊ ጥያቄም ተሰምቶ ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል። አሁን ላይ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ በመኾኑ ያመሰገኑት ወይዘሮ ወርቅነሽ የሸቀጥ ዋጋ መናር፣ ለመስኖ ልማት የሚፈልጉት ነዳጅ የሚገኘው በጥቁር ገበያ መኾኑ እና በማደያዎች ያለው እንግልት እና ወከባ እንዲስተካከል ጠይቀዋል።
በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ሃብታሙ አላምረው ባለፉት ስምንት ወራት የተሠሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እና በቀጣይ መሠራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ስለመደረጉ አስገንዝበዋል፡፡ የመልካም አሥተዳደር ችግር የሁሉም ችግሮች ምንጭ መኾኑን ኅብረተሰቡ ስለማንሳቱም ነው የተናገሩት፡፡ በቀጣይም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ነው የገለጹት።
የቤቶች እድሳት እና የመንገዶችን ተፋሰስ ጠረጋ በመሥራት በመጪው ክረምት የሚኖረውን ችግር ለመቀነስ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ሕዝቡም ሰላሙን በባለቤትነት እንዲጠብቅ ውይይቶች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀምም ልማት ተጠናክሮ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!