
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ከጣና ሐይቅ በስተ-ምሥራቅ በኩል በሊቦ ከምከም እና በፎገራ ወረዳዎች ውስጥ ነው የታችኛው ርብ መስኖ እና ድሬይኔጅ ፕሮጀክት የሚገኘው። በ1 ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በ2016 በጀት ዓመት ሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 92 ነጥብ 06 በመቶ ደርሷል፡፡
ፕሮጀክቱ ታኅሣሥ/2017 ዓ.ም መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ታቅዶም ነው እየተሠራ የሚገኘው፡፡ ፕሮጀክቱ በ2008 በጀት ዓመት የተጀመረ እና በአንድ የቻይና ሥራ ተቋራጭ ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ከጥቅምት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም ባንክ የብድር ጊዜ ስለተጠናቀቀ ከበፊቱ ተቋራጭ ጋር ውል እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
በመኾኑም መንግሥት በራስ አቅም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የመስኖ አውታርና ተያያዥ የግንባታ ሥራዎችን ከዓባይ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር ውል በመግባት እያሠራም ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 3 ሺህ 320 ሄክታር የማልማት አቅም ያለው ነው፡፡ በቀኝ በኩል 861 ሄክታር በግራ በኩል 2 ሺህ 459 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 6 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚም ያደርጋል፡፡
የፀጥታ ችግር፣ የካሳ ክፍያ ፣ ጊዜያዊ እና መሰረታዊ የወሰን ማስከበር እንዲሁም የተገነቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረስ የፕሮጀክቱ ተግዳሮቶች መኾናቸውን ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ችግሮቹን ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያስገነባው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሲኾን በሥራ ተቋራጭነት የሚገነባው ዓባይ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ስለመኾኑም ነው የተብራራው፡፡ የማማከሩን እና የቁጥጥር ሥራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐርቭዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!