
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማኞች የቤተክርስቲያኒቷ “መንፈሳዊ ትጥቆች” ተደርገው የሚወሰዱትን ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መተጋገዝ እና አብሮነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የሃይማኖት አባቶች ተናግረዋል፡፡ የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴዴራል ስብከት ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር ቃለጽድቅ አየነው እንዳሉት ጾም የሰው ልጅ ከሚበላ እና ከሚጠጣ ብቻ ሳይኾን ከክፉ ነገር ሁሉ የሰውነት ሕዋሳትን አቀናጅቶ በአንድ እንዲሠራ የሚያደርግ የሕግ መነሻ ነው ይላሉ።
መምህር ቃለጽድቅ እንዳሉት ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በጾም ሲኾን ያጠናቀቀው ደግሞ በመስቀሉ ላይ ራሱን በመሥጠት ባሳየው ፍቅር ነው። በመኾኑም ጾም የሕግ መነሻ ነው፤ ፍቅር ደግሞ የሕግ ፍጻሜ መኾኑን ገልጸዋል። “ትሕትና፣ ፍቅር እና የይቅርታ ልብ ሳይኖር የሚጾም ጾም በቆሸሸ ሳህን እንደሚቀርብ ምግብ ይቆጠራል” ይላሉ መምሕሩ። ንጹሕ ምግም በቆሸሸ ሳህን ከቀረበ ለጤና ችግር ነውና። በመኾኑም አማኞች የቤተክርስቲያኒቷ “መንፈሳዊ ትጥቆች” ተደርገው በሚወሰዱት ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ትሕትና፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መተጋገዝ እና አብሮነት ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ መክረዋል መምህሩ።
ትሁት መኾን አምላክን ለማስታወስ ይጠቅማል፤ ማማረርንም ያስወግዳል ነው ያሉት። እባብ ተቀላቅሎ ራሱን እንዳያጠፋው መርዙን ተፍቶ ውኃ እንደሚጠጣው አማኞችም ጾሙን ሲጾሙ የሰውን ልጅ ከሚመርዙ መጥፎ ነገሮች በመራቅ ሊኾን ይገባል ብለዋል። የሚጾመው ጾም ትዕቢት ካለበት በመርዝ የተለወሰ ምግብ እንደመብላት ይቆጠራል ሲሉም ተናግረዋል።
ጾም የተቸገሩ ሰዎችን ስሜት አውቆ ለመረዳት እና በጾም ወቅት የታለፈው ምግብ ለተቸገሩ ወገኖች ለማበርከት የሚጠቅም ስለመኾኑም አንስተዋል። መተጋገዝ ሲዳብር ደግሞ አብሮነትን፣ ዝምድናን ያጠናክራል። መምሕሩ መልካምነት በጾም ብቻ ሳይኾን ሁልጊዜ ሳይቋረጥ የሚተገበር በመኾኑ ደካሞችን በገንዘብ፣ በጉልበት እና በዕውቀት ማገዝ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!