የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ፡፡

14

እንጅባራ: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ከ19 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ቡድን መሪ ልየው ገሰሰ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የምርት ዝውውር በመገታቱ በግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።

በሰላም መደፍረሱ ምክንያት በንግድ ሥርዓቱ ሕጋዊ አሠራሮች መላላት ታይቶባቸዋል፤ ሕገ ወጥ እና የኮንትሮባንድ ንግድም ተበራክቷል ነው ያሉት። ይህም በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ ባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሊቋቋሙት የማይችሉት የኑሮ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።

የዋጋ ንረቱ በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ በሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ እስከ በጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ድረስ 19 ሺህ 423 ኩንታል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከዚህ በላይ ለመሥራት ታቅዶ የነበረ ቢኾንም የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለባቸው የፋይናንስ እጥረት እና የመንገዶች በተደጋጋሚ መዘጋት ባቀዱት ልክ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት ፈጥሯልም ነው ያሉት። የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት መቅረፍ፣ ሸማች ተኮር ግብይት ማስፋፋት እና ሕገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን መከላከል ቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አቶ ልየው አንስተዋል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleረመዷንን በመረዳዳት እና በመደጋገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።
Next articleአማኞች የቤተክርስቲያኒቷ “መንፈሳዊ ትጥቆች” ተደርገው የሚወሰዱትን ጾም፣ ጸሎት እና ምጽዋት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡