
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ረመዷን የሰደቃ ወር ተደርጎ ይወሰዳል። ሃብታሞች ደሆችን፤ አቅም ያላቸው አቅመ ደካሞችን የሚጠይቁበት ወርም ነው። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና ዳዕዋ ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም እንዳሉት ረመዷን ረሃብ እና የውኃ ጥም ምን እንደኾነ የሚታይበት ወር በመኾኑ የተቸገሩ ሰዎችን ለማስታዎስ እድል የሚፈጥር ነው።
ረመዷን የሰደቃ ወር በመኾኑ አቅመ ደካሞችን፣ ተፈናቃዮችን እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማገዝ ረመዷንን እንዲያሳልፉ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም እንዳሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ለፈጣሪው ታማኝ ለመኾኑ ከለፋበት ቀንሶ ለምስኪን መስጠት የአማኙን እምነት የሚያጎላ ብቻ ሳይኾን ለማስረጃነት ማሳያ እንደኾነ ሃይማኖቱ ያስተምራል። ሰደቃ የእውነት እና የታማኝነት መገለጫ በመኾኑ ሁሉም በዚህ የተከበረ ወር ምስኪኖችን መጠየቅ፣ ማገዝ እና መደገፍ ይገባል ብለዋል።
በረመዷን ወር በቻግኒ አካባቢ የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ በማሠባሠብ በየቀኑ እስከ 1 ሺህ የተቸገሩ ወገኖች እያስፈጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከማኅበረሰቡ ባለፈ በአካባቢው የሚገኙ እንደ አቢሲኒያ እና አዋሽ የመሳሰሉ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ እና በቁሳቁስ በማገዝ የተቸገሩ ወገኖችን የማስፈጠር ሥራ መሠራቱንም ነው የገለጹት።
በገርባ፣ በሰሜን ወሎ ጃራ፣ በሐይቅ፣ በሰሜን ሸዋ እና በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮችም የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አንስተዋል። ይሁን እንጅ ካለው ችግር ስፋት አኳያ ማኅበረሰቡ ድጋፉን በማጠናከር ሕይዎት የመታደግ ሥራውን እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትም ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን ለማገዝ የራሱን ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ሃብት የማሠባሠብ ሥራም እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡም ምክር ቤቱ በከፈታቸው የሂሳብ ደብተር ቁጥሮች (አካውንት) ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!