
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ውኃ ሃብት እና ሰፊ መልማት የሚችል የእርሻ መሬት እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ። ከፍተኛ የውኃ ሃብት እና ሰፊ መልማት የሚችል የእርሻ መሬት ካላቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ምዕራብ ጎንደር ዞን ተጠቃሽ ነው።
የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ እንደሚያሳየው ዞኑ ካላው አጠቃላይ ከ1 ሚሊዮን 900 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ655 ሺህ በላይ ሄክታሩ መታረስ የሚችል መሬት ነው። በተለይ ደግሞ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችሉ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ግብዓት እና ገበያ ተኮር ሰብሎችን እንዲኹም እጣን እና ሙጫ በማምረት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
የምዕራብ ጎንደር ዞን መስኖ እና የቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ዓለምነው እንዳሉት በዞኑ ሊታረስ ከሚችለው መሬት 290 ሺህ ሄክታሩ በመስኖ መልማት የሚችል ነው። ለአካባቢው ባይተዋር የኾኑ 31 በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሚፈስሱ ወንዞች እና ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት ባለቤትም ነው፡፡ አካባቢው ይህን ያህል በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እና የውኃ ሃብት ቢኖረውም አሁን ላይ እየለማ የሚገኘው ግን ከ2 ሺህ 150 ሄክታር መሬት አይበልጥም። ይህም በባሕላዊ መንግድ የሚለማ እንደኾነ አቶ ሹመት ነግረውናል።
በዞኑ የሚገኙ ወንዞችን በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ለልማት ለማዋል ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በክልሉ ልህቀት እና ዲዛይን ቁጥጥር ኮርፖሬሽን እየተጠና የሚገኘው የሽንፋ ወንዝ አንዱ ነው። የኮርፖሬሽኑ ኀላፊ እንዳሉት የሽንፋ ወንዝ ፕሮጀክት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ጥናት ሲደረግ ቢቆይም በአካባቢው በተከታታይ ተከስቶ በነበረው ግጭት ሊቋረጥ ችሏል። በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ዳግም በ2015 ዓ.ም ወደ ሥራ ተገብቶ የጥናቱን 38 በመቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ በ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ዳግም ጥናቱ መቆሙን ገልጸዋል። አሁን ላይ አካባቢው ሰላም መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ልህቀት፣ ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ወደ አካባቢው ገብቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል። ማኅበረሰቡ የፕሮጀክቱ ባለቤት ኾኖ ሥራውን እንዲያግዝ መምሪያው እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የልህቀት፣ ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ውኃ መስኖ እና ኢነርጅ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹምየ ኃይለማርያም እንዳሉት እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል። ወንዞችን በመገደብ ለልማት ማዋል ደግሞ አንዱ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ባለቤትነት እና በአማራ ክልል ልህቀት፣ ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን አማካሪነት በምዕራብ ጎንደር ዞን የሽንፋ ሜጋ ፕሮጀክት ጥናትን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ጥናቱ በአካባቢው በተከታታይ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለአራት ዓመታት ተቋርጦ መቆየቱን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ሥራው የሁለት ዓመት ማራዘሚያ ጊዜ ተሰጥቶት በ2015 ዓ. ም በነበረው ሰላም የጥናቱ ምዕራፍ አንድ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸውልናል። ይሁን እንጅ በዚህ ዓመት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር እስከ አሁን ወደ ሥራ አለመገባቱን ነው የገለጹት። አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ቀሪ ጥናቱን እስከ 2017 ዓ.ም አጋማሽ አጠናቅቆ ለማስረከብ ታቅዷል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የርጭት መስኖ የሚባለው ዘመናዊ መስኖ ሲኾን ግንባታው 12 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል። ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ 85 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው። ከ92 ሺህ በላይ ዜጎችንም ቀጥተኛ ተጠቃሚ ያደርጋል። ከዚህም ባሻገር ሰፊ ቁጥር ያለውን ማኅበረሰብ በንግድ ትስስር ተጠቃሚ ያደርጋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!