የ30 ሜትር ስፋት ያለው አስፋልት ቀለበት መንገድ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

29

ወልድያ: መጋቢት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥራ ኀላፊዎች የወልድያ ከተማ አሥተዳደር እየሠራቸው ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከጎንደር በር – ፒያሳ – ደብረ ገሊላ በፌደራል መንግሥት በጀት እየተሠራ ያለው መንገድ የመጀመሪያ ዙር የአስፋልት ንጣፍ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የፌደራል በጀት አካል የሆነው ወደ ሼህ ሙሐመድ አሊ አላህሙዲን ስታዲየም መግቢያ እና መውጫ የሚገነቡት ሁለት መንገዶች ደግሞ ለአስፋልት ንጣፍ የማመቻቸት ሥራ በዚህ ዓመት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ሙሉ በጀት የሚሠራው 30 ሜትር ስፋት ያለው የአስፋልት ቀለበት መንገድ በሦስት ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የትምህርት ቤት እና የጤና ጣቢያ ግንባታዎችን ገንብቶ ማጠናቀቁን ከንቲባው በጉብኝቱ ወቅት አስረድተዋል።

የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እና የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦንት ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ከንቲባው ኅብረተሰቡ የልማት ሥራዎችን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የፈጸማቸው እና በግንባታ ላይ ያሉ የልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን በጉብኝታቸው እንደታዘቡ የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ታደሰ ግርማው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምሥጋና 🙏
Next articleበኩር ጋዜጣ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም ዕትም