ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሪፎርም ሥራ መጀመሩን የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለጸ።

15

ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እድገት የማይተካ ሚና አላቸው።

የተለያዩ ሀገራት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት በሰጡት ትኩረት በሀገራዊ ጥቅል ምርት (GDP) ላይ እንደ አንድ ተዋናይ ኾነው ያገለግላሉ።

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ማኅበራት ያላቸውን ፋይዳ ለማሳየት የጎረቤት ሀገር ኬንያን ተሞክሮ በማሳያነት ማንሳት ይቻላል።

በኬንያ ከጠቅላላው 52 ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ 63 በመቶው በኅብረት ሥራ ማኅበር የተደራጀ እንደኾነ ይነገራል። ሀገሪቱ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ በሠራችው ውጤታማ ሥራ የአባላትን ተጠቃሚነት እና የቁጠባ ባሕልን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ችላለች። ከአጠቃላይ ከሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርትም (GDP) ከ43 እስከ 45 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይነገራል።

በአማካይ በኬንያ አንድ የኅብረት የሥራ ማኅበር ከ1 ሺህ 300 በላይ የሥራ እድል መፍጠር ይችላል። በዚህም የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለሥራ እድል መፍጠሪያነት ተጠቅማበታለች።

አቶ ጌትነት የሕንድን ተሞክሮም አንስተዋል። በሕንድ 50 በመቶ ሕዝብ በገንዘብ፣ ቁጠባ እና ብድር ማኅበራት የተደራጀ ነው። ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተለይም ደግሞ በግብዓት እና ግብይት ሥራው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው። በኅብረት ሥራ ለተደራጁ ማኅበራት የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ኮኦፕሬቲቭ ባንክ ሥርዓት እስከ ወረዳ ዘርግተዋል። ባንኩ 67 በመቶ የሚኾነውን የሸማቾችን ፍላጎት እንደሚያቀርብ የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ኀላፊው እንዳሉት በኢትዮጵያ 110 ሺህ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚገኙ ሲኾን ዓመታዊ የጥቅል ምርት (GDP) ድርሻቸው 12 በመቶ ብቻ ነው።

በአማራ ክልል ደግሞ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባላት ያቀፈ 29 ሺህ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ። ማኅበራቱ ሰዎች በተናጠል የማይፈቷቸውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በጋራ በመኾን ከመፍታት ባለፈ ከአባላት ውጭ ለኾነው የኅበረተሰብ ክፍልም የገበያ ማረጋጋት፣ ግብዓት በማሰራጨት ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህ ዓመት ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር ተመቻችቶላቸው የገበያ ማረጋጋት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በክልሉ 1 ሺህ 900 ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና 23 ዩኒዮኖች 99 በመቶ የሚኾነውን የማዳበሪያ ግብዓት እያቀረቡ ይገኛሉ። አርሶ አደሮች ያመረቱትን ለገበያ በማቅረብ እና እሴት በመጨመር የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በገንዘብ፣ ቁጠባ እና ብድር የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙም አቶ ጌትነት ገልጸዋል። ማኅበራቱ ዘግይተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ያነሱት አቶ ጌትነት የአባላቱን ተጠቃሚነት በማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፤ የቁጠባ ባሕል እንዲያድግ ማድረጋቸውንም አንስተዋል። ኅብረት ሥራ ማኅበራት 19 በመቶ የክልሉን የዘር ፍላጎት መሸፈን መቻላቸውን አንስተዋል።

ኅብረት ሥራ ማኅበራት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ ቢገኝም በአደራጅ ተቋሙ ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ዝቅተኛ መኾን፣ ማኅበረሰቡም ስለ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መኾን፣ ማኅበራትን በሰለጠነ የሰው ኃይል ሙሉ በመሉ እንዲመሩ አለማድረግ፣ በተቋቋሙለት ዓላማ መሠረት አለመሥራት፣ የሚያንቀሳቅሱት ካፒታል እና የማኅበራት ቁጥር አለመመጣጠን የመሳሰሉ ችግሮች መኖሩን አንስተዋል።

ማኅበራቱ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ፣ የአባላት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ የግብይት አቅማቸውን፣ የብድር ሥርጭት እና ቁጠባ አቅማቸውን ለማሳድግ፣ የአደራጅ ተቋሙን ድጋፍ እና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ እና መሰል ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ የሪፎርም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። ሪፎርሙ ደረጃ በደረጃ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ማኅበራት ልምድ በመውሰድ እንደሚሠራም ተጠሟል።

ለውጤታማነቱ የማኅበራት ሠራተኞቹ፣ በየደረጃው የሚገኙ አደራጅ ተቋማት እና ሌሎች አጋር አካላት ባለቤት እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገር ቀንዲል ጸሐፊ ትዕዛዛት አክሊሉ ሐብተወልድ
Next articleምሥጋና 🙏