
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በያዝነው ሳምንት 1953 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነው የተሾሙትን ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ ትዕዛዛት አክሊሉ ሐብተወልድን እንቃኛለን፡፡
ጸሐፊ ትዕዛዛት አክሊሉ ሐብተወልድ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ዲፕሎማሲ ታሪክ ስመ ጥር ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ ሀገራቸውን ከፍ ለማድረግ በተደረገው እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ትግል ጣሊያንን ጨምሮ ከሌሎች ኃያላን ሀገራትም አንገት ላንገት ተናንቀው በድል የተመለሱ የኢትዮጵያ ቀኝ ክንድ በመባልም ይታወቃሉ፡፡
ጸሐፊ ትዕዛዛት አክሊሉ ሐብተወልድ የተወለዱት በ1904 ዓ.ም ነበር፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለጥረት፣ ለዕውቀት እና ለስኬት የተመረጡት፤ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ያለመሰልቸት ያገለገሉት እና በዘመናዊ አሥተዳደርም በመንግሥት ልዑክነት ሥራ ኢትዮጵያ ከወቅቱ የአውሮፓ ኃያላን ጋር በተፋጠጠችባቸው የዲፕሎማሲ ትግሎች ቀጥ ብለው የተፋለሙ እና ድል የተቀዳጁም ስለመኾናቸው ይነገራል፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት የሕግ፣ የምጣኔ ሃብት እና የፖለቲካ ትምህርት የቀሰሙት የጸሐፊ ትዕዛዛት አክሊሉ ሐብተወልድ፡-
👉 ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገቢውን ክብር እና ጥቅሞች እንድታገኝ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለ እረፍት ተጋድሎ አድርገዋል፡፡
👉 ከጣሊያን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ጥቅም፣ ክብር እና መብቶች ለማስጠበቅ በነጮች መድረክ ብቻቸውን ተገኝተው ሞግተዋል፡፡
👉 በዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊጎፍኔሽን) የኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ኾነው ያገለገሉ ሲኾን፤ በአፋምቦ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላ እና በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ከነበሩ ቅኝ ገዢ ሀገራት ግዛትነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
👉 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመሠራረት እና አሥተዳደር አኳያም የእንግሊዝ ንግሥት አቀረቡት የተባለውን በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንዲተዳደር የመፈለግ አዝማሚያ “እኛ የናንተ ቀኝ ተገዢዎች አይደለንም” በማለት ተከራክረው የኢትዮጵያን በባንክ አሥተዳደር ራሷን ማስቻላቸው ሁሌም ስማቸው ከፍ ብሎ እንዲነሳ የሚያደርጋቸው ሥራቸው ነው፡፡
👉 በባንክ፣ በአየር መንገድ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የሚያዘምኑ ሥራዎች ላይ ዋና ተዋናይ በመኾን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች በመወከል እንዲሁም ለጥቅሟ በመሟገት ዘብ የቆሙ ታላቅ የዲፕሎማቲክ ሰውም ናቸው፡፡
ክቡር ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ለሀገራቸው በርካታ አስተዋጽኦ ካበረከቱበት ኃላፊነታቸው ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነው የተሾሙት በያዝነው ሳምንት መጋቢት 20 ቀን 1953 ዓ.ም ነበር፡፡
—-/////——/////——–//////——
የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሳሁን
እኒህን ጀግና ሴት በዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ዝግጅታችን ለመጀመረያ ጊዜ “ትዳር በዘዴ” የተሰኘ መጽሐፋቸውን ለእንባቢያን በዚህ ሳምንት ያበቁበትን ምክንያት በማድረግ የሕይዎት ታሪካቸውን እንዳስሳለን፡፡
ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና ጸሐፊ ትውኔት ሮማነወርቅ ካሳሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዓለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደግመዋል።
ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተምረዋል። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን “ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም” የሚለውን ልማድ በጥረታቸው እና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር። በወቅቱ በነበረው ልማድም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ትዳር ይዘው የአንዲት ሴት ልጅ እናት ኾነዋል።
ሮማነወርቅ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅት ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናት እና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደ አደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በ1939 ዓ.ም በወቅቱ “የማስታወቂያ እና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ በነበረው መሥሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመኾን ተቀጠሩ።
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በተሰጣቸው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥራቸው የተለያዩ ጽሑፎችን እና ዜናዎችን በማዘጋጀት በማራኪ አንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት በዜና አቀራረባቸው እና በፕሮግራም ዝግጅታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እና አድናቆትን ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።
ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሠርተዋል። በወቅቱም ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው በዝግጅቶቻቸው ላይ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎችን በማቅረብ ሕዝቡን ሲያገለግሉ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩት ሴቶች ልጆች እንደብርቅዬ እና የበጎ ተግባር ምሳሌ በመኾን ይታዩ ነበር።
በዝግጅቶቻቸው የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በወቅቱ በሴቶች ዘንድ ጫና የሚፈጥሩ አመለካከቶችን ለመቅረፍ በመገናኛ ብዙኅን የራሳቸውን እና የብዙ ሴቶችን ድምፅ አሰምተዋል።
የሴቶች ማኅበራዊ ሕይዎት መሻሻል ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችንም ይጽፉ ነበር። ከሥራዎቻቸው መካከል የበኩር ሥራቸው የተጠናቀቀው በ1940 ዓ.ም ቢኾንም መጽሐፋቸውን ይዘው ወደ ሕትመት የሄዱት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1942 ዓ.ም ነበር። ይህንን ጉዳይ አስመልክተውም በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ በማለት ስለሕትመቱ ጉዳይ በትህትና ገልጸዋል።
“መጽሐፌን ጽፌ የጨረስኩት በ1940 ዓ.ም ነበር። ከዚያ ወዲህ ሁለት ዓመታት ቆይቼ ሳነበው ከእርሱ የተሻለ ለመፃፍ የምችል ኾኖ ተሰማኝ። በዚህ ምክንያት ተሳንፌ ማሳተሙን ለማቆየት ከቆረጥሁ በኋላ የሰው እውቀት የዕድሜ ደረጃን ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ አዋቂ አለመኾንን በማሰብ ዛሬ የተሻለ መስሎኝ ብሠራም ነገ መናቄ እንደማይቀር ተረዳሁት። ይህም የሰው አዕምሮ ያለማቋረጥ የሚሻሻል ለመኾኑ ዋና ማስረጃ ነው በማለት ይህን ሁሉ ካወጣሁ እና ካወረድሁ በኋላ ማመንታትን ትቼ አሳተምሁት” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በያዝነው ሳምንት የመጀመሪያ ሥራቸውን ለአንባቢ ያቀረቡት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ርዕስ “ትዳር በዘዴ” የሚል ነበር። መጽሐፉ የገጠሩን እና የከተማውን ትዳር እና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲኾን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀርባል።
ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉ ደራሲ “ለትዳር ፈላጊዎች ምክር አለኝ” በማለት ስለትዳር የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸው ጫናም በመጽሐፉ ተዳስሷል። ከዚያ በኋላም በርካታ የጋዜጣ መጣጥፎችን እና መጻሕፍትን ጽፈዋል። በሥራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ጋዜጠኛ፣ ደራሲ እና ጸሐፊ ትውኔት ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው 1964 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ጋዜጠኛዋ ሞት ቀደማቸው እንጂ “ሔዋን”፣ “መልካም እመቤት”፣ “የቤተሰብ አቋም”፣ “የባልትና ትምህርት”፣ “የሕፃናት ይዞታ”፣ “ዘመናዊ ኑሮ”፣ “የኑሮ መስታወት”፣ “ጋብቻና ወጣቶች”፣ እንዲሁም “የባልና የሚስት ጠብ” በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ታሪካቸው ያሳያል።
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!