“በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ በ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የንፁህ መጠጥ ውኃ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)

41

ደብረ ብርሃን፡ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጫጫ ክፍለ ከተማ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ዛሬ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በመበጀት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በአማራ ክልል እየተገነቡ ያሉ የውኃ ተቋማት በአግባቡ እንዳይሠሩ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት እንቅፋት ኾኗል ሲሉ ዶክተር ማማሩ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ እና በአማራ ክልል መንግሥት ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የገንዘብ ድጋፍ እና ትብብር ነው የተገነባው። የውኃ ፕሮጀክቱ በ71 ሚሊዮን ብር መገንባቱን የከተማ አሥተዳደሩ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሰረት መንገሻ አስታውቀዋል። ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የኾነው የውኃ ፕሮጀክት ከ12 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የተመረቀውን የውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በአግባቡ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ማኅበረሰቡ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ዮናስ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተማሪ ምገባ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleየስናን ወረዳ ነዋሪዎች መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ችግሮቻቸውን እንዲፈታላቸው ጠየቁ።