እያጋጠሙ ያሉ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈቱት በጦርነት ሳይኾን በውይይት ሊኾን እንደሚገባ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

38

ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ መልእክት ከከተማው ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ያለመ ውይይት ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተካሂዷል፡፡ አሁን እያጋጠሙ ያሉ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈቱት በጦርነት ሳይኾን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከመገፋፋት ይልቅ በእርቅ እና በይቅርታ ሰላም እንዲሰፍን መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ከተማ አሥተዳደሩ የዋጋ ንረትን እና ማኅበረሰቡን ያማረሩ የመልካም አሥተዳደር እንዲሁም የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ላቀች ሰማ አሁን እየታየ ያለው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነቱ የሚረጋገጠው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ለሕዝቡ ተገቢ አገልግሎት መስጠት ሲችሉ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር በመኾን የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው ከማኅበረሰቡ የሚነሱ ችግሮች የሚፈቱት ዘላቂ ሰላም ተረጋግጦ፣ በአንድነት በመነጋገር ሰላማዊ ትግል ማድረግ ሲቻል እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ በሁሉም አካባቢ ልማት እንዲቀጥል ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾንም ጠይቀዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ በየጊዜው የተደረጉ ሕዝባዊ የምክክር መድረኮች አሁን እየታየ ላለው አንፃራዊ ሰላም ድርሻቸው የጎላ እንደነበርም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ወንድወሰን ዋለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት ተዋግቶ በማስወገድ ገዥ እና የጋራ ትርክትን ለመትከል እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረግን ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleበተማሪ ምገባ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።