
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ መልእክት ክልላዊ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችን ጠቅሰው በተለይም ባለፉት ወራት በክልሉ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ አንስተው በዚህም ሕዝቡ መጎዳቱን ገልጸዋል። የሰላም እጦቱን ተከትሎ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፤ ጽንፈኛ አካላት ነፃ የንግድ እንቅስቃሴን እየገደቡ፣ የማዳበሪያ ስርጭትንም እያስተጓጎሉ በሕዝብ ላይ ችግሮችን እየደራረቡ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ተቋማት እና በሕዝቡ ርብርብ አንጻራዊ ሰላምን ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል። ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ በሚል ሰበብ የራሳቸውን ጥቅም ለማጋበስ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን አካሄድ መረዳት እና ለዘለቄታው በቃችሁ ማለት ይገባል ነው ያሉት።
“ሕዝባችን ግጭት ሰልችቶታል፤ ጦርነትም ጠልቷል” ያሉት አቶ ይርጋ የሕዝብ ጥያቄ ልማት እና ችግሮችን በሰላም መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አቶ ይርጋ “ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት ተዋግቶ በማስወገድ ገዥ እና የጋራ ትርክትን ለመትከል እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረግን ነው” ሲሉም ተናግረዋል። አሁን ላይ አማራ ክልል ጽንፈኞች በፈጠሩት ችግር ገፈት ቀማሽ እየኾነ ነው፤ ይህንን በዘላቂነት አርሞ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሁሉንም የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
“ማኅበረሰቡ ሌብነት እና ወንጀል አንገብግቦታል” ያሉት አቶ ይርጋ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ወደ ሰላም እንዲመለሱ አብዝቶ እየጎተጎተ ስለመኾኑ ተናግረዋል። አሻፈረኝ ብለው ሽፍትነትን በመረጡት ላይ ደግሞ መንግሥት እርምጃ ወስዶ ሕግ እንዲያስከብር ሕዝቡ መንግሥትን እየጠየቀ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ፓርቲ የሰላም እና መልካም አሥተዳደር መስፈንን ጨምሮ ሌሎችንም ዋና ዋና የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። አማራ ክልል በርካታ እምቅ ሃብት አለው፤ በጋራ አስበን፣ አቅደን እና ተናብበን በመሥራት የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ እና የመልማት ጥያቄዎችንም ለመመለስ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉም ተናግረዋል። የሚገጥሙ ችግሮችን በብልሃት እየፈታ ለሀገር ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ፓርቲ እና አመራር የመገንባት ሥራም በትኩረት ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!