“የሕዝብ ጥያቄዎች የደረሱበትን እንገመግማለን፤ የቀሩንን በአጭር ጊዜ ለመሥራት ልዩ ርብርብ እናደርጋለን” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

60

ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከመጋቢት 21/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ክልላዊ ኮንፈረንስ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ክልላዊ ኮንፈረንሱን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ኮንፈረንስ እየተካሄደ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በፈተናዎች ውስጥ ኾኖ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኝ አካታች እና ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲው በፕሮግራሙ የሀገሪቱን የቆዩ ቁርሾዎች የሚፈቱ፣ መጻዒ እድገት የሚወስኑ፣ የሕዝቦችን አንድነት እና አብሮነት የሚያስተሳስሩ እሳቤዎችን ቀርጾ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የበለጠ እየጎለበቱ የሚሄዱ እሳቤዎችን ይዞ የተነሳው ፓርቲው ለሁለንተናዊ ብልጽግና ትልም ሊያረጋግጡ የሚችሉ ውሳኔዎች ማሳለፉንም አስታውሰዋል፡፡

ከቀበሌ እስከ ዞን እና ከተማ አሥተዳደር ድረስ ሲካሄድ የቆየው ኮንፈረንስ ከመጋቢት 21/2016 ዓ.ም እስከ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም ክልላዊ የማጠቃለያ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡ በኮንፈረንሱ ከ1 ሺህ 500 በላይ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት ይሳተፉበታል ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የመንግሥትን አፈጻጸም፣ የፓርቲውን አባላት እና መሪዎች ሚና አንጥሮ በማየት ከነበረው ሂደት ትምህርት በመውሰድ ድክመቶችን በማረም ለቀጣይ የርብርብ ማዕከላትን ለመለየት ዓላማ የያዘ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ ፓርቲው የወደፊቷን ኢትዮጵያ ተረድቶ ለወደፊት ሕልውና እና ሁለንተናዊ አንድነት በርካታ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

ፓርቲው በምርጫ ለሕዝብ ቃል የገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሱት ኀላፊው በማኒፌስቶው ያስቀመጣቸውን በርካታ ተግባራት በአግባቡ በማየት፣ የቀሩ ሥራዎች የሚገመግምበት ቆይታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ኮንፈረንሱ የእስካሁኑ አፈጻጸሞቹ የሚገመገሙበት እና የወደፊት አቅጣጫ የሚቀመጥበት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የታቀዱ የልማት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በአግባቡ በመገምገም፣ የመንግሥትን መዋቅር በአግባቡ በማየት፣ በሕዝብ ውስጥ እየተጠፈጠሩ ያሉ ንቅናቄዎችን በመቃኘት ለቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣልም ብለዋል በመግለጫቸው፡፡ የታቀዱ እቅዶችን እና የተለዩ ማሳለጫ መንገዶችን በአግባቡ በመለየት በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ፣ በሰላም ግንባታ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ እና በውጭ ጉዳይ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የተገኙ ውጤቶችን እና ተግዳሮቶችን በአግባቡ በመገምገም በቀጣይ ጊዜያት ለመፈጸም የሚያስችል ጠለቅ ያለ ውይይት ይካሄዳል ነው የተባለው፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት በክልሉ በጽንፈኛ ኃይሎች የተፈጠረው ቀውስ ተቀልብሶ በሁሉም አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም አለ ያሉት ኀላፊው የፀጥታ ሁኔታውን በአግባቡ በመገምገም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ ይመክራል ብለዋል፡፡ ሕዝቡን በማደረጃት ራሱ የሰላም ባለቤት በሚኾንበት ሁኔታ ከፀጥታ ሁኔታው በአጭር ጊዜ በመውጣት ፊቱን ወደ ሰላም እንዲያዞር በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይም ይመክራል ነው የተባለው፡፡ በየደረጃው የሚፈጠሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በማረም የሕዝብን እንግልት መቀነስ በሚቻልባቸው ሁነቶች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ውይይት ይደረጋልም ተብሏል፡፡

ከምርጫ ማግስት የመጣንባቸውን፣ የአቀድናቸውን የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአግባቡ በመገምገም በጥራት እና በጥንካሬዎች ላይ በመግባባት፣ እጥረቶችን በአጭር ጊዜ በመቅረፍ፣ ክልላዊ ለውጥ ለመፍጠር ጥቅል ዓላማ አድርገን ክልላዊ ኮንፈረንሶችን እናካሂዳለን ብለዋል፡፡

ከኮንፈረንሱ ነጥረው የሚወጡ ሃሳቦችን እና አቋሞችን በመያዝ በቀሪ ጊዜያት በርብርብ የሚሠሩ ሥራዎች ይለያሉ ነው ያሉት፡፡ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት በፓርቲው ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ውይይት እናካሂዳለን ብለዋል፡፡ በፓርቲው የተቀመጡ ግቦች እና ራዕዮችን እንደሚገመግሙም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ጥያቄዎች የደረሱበትን እንገመግማለን፣ የቀሩንን በአጭር ጊዜ ለመሥራት ልዩ ርብርብ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው መሪዎች እና አባላት በፓርቲው ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው እና ውስጣዊ አንድነት መፍጠር ከኮንፈረንሱ የሚጠበቅ ጉዳይ መኾኑን አመላክተዋል፡፡
በየደረጃው ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ከኮንፈረንሱ የሚጠበቅ ሌላኛው ውጤት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለሌላው ዓርአያ የሚኾኑ እና ሚዛን የሚስጠብቁ ውይይቶች በየደረጃው እንደሚካሄዱም አስታውቀዋል፡፡

በየደረጃው የተፈጠረው ጠንካራ መሪ እና አባል ምን ያክል መንግሥትን አጠናክሯል? ልማትን አፋጥኗል? ተገልጋዮችን አርክቷል? ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም አስተዋጽኦ አበርክቷል? በሚሉ እና የሕዝብ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳይች ዙሪያ ውይይት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ጉዳዮችን ለማካካስ በፍጥነት መሥራት ይጠብቃል ነው ያሉት፡፡ ከመደበኛው በወጣ አሠራር ሁኔታ መፍጠን እና መፍጠር ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

አሁን ያለው የጽንፈኛ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን አስተናግደናል ያሉት ኀላፊው በመጣንበት ምዕራፍ ፈተናዎች ሳይበግሩን ተጉዘናል ነው ያሉት፡፡ ፈተናዎች ወደ እድል የሚወስዱን እንጂ ወጀብ ኾነው የሚያስወስዱን አይደሉም ብለዋል፡፡ ወደፊትም ይሄ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

በኮንፈረንሱ የታቀዱ እቅዶች መሬት በሚነኩበት ዙሪያ በመግባባት የሚደረስበት እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ ጠንካራ ትስስር እና መስተጋብር በመፍጠር ኃይል የማሰባሰብ፣ ችግሮች ሁሉ በሰላም እንዲፈቱ የማድረግ ውይይት ይካሄዳል ነው የተባለው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንጂ በጽንፈኝነት አካሄድ በመሣሪያ የሚፈታ ምንም ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአፈሙዝ የሚፈታ ነገር እንደሌለ ተረድተው ወደ ሕዝብ እና መንግሥት መመለሳቸውን የታጠቁ ኃይሎች ገለጹ፡፡
Next articleየሴቶችን ተሳታፊነት እና ውሳኔ ሰጭነት ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡