
ባሕር ዳር: መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የአማራነት ጥያቄ አለን በሚል ሽፋን ትጥቅ አንግበው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች በሰላም እጃቸውን ለወረዳው ኮማንድፖስት እየሰጡ እንደኾ ተገልጿል።
የታጣቂ ኃይሉ ሠብሣቢ እሸት ዓለሙ እና ፈንታሁን አስናቀው የአማራ ጥያቄዎች በትጥቅ ትግል ይፈታሉ በሚል ጫካ ስለመግባታቸው ተናግረዋል።
ሰላም በጦርነት አይመጣም ያሉት ታጣቂዎቹ ከሁለቱም በኩል ያለውን በማየት እና በመገንዘብ በአፈሙዝ የሚፈታ ነገር እንደሌለ ተረድተው ከሕዝባቸው ጎን ኾነው ቢመክሩ የተሻለ ስለመኾኑ ነው ያስረዱት፡፡ የኮማንድፖስቱ የሰላም ጥሪ ከተላለፈ በኋላ ዛሬ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም የገቡትን 16 ታጣቂዎች ጨምሮ 57 ያህል ታጣቂዎች በሰላም ገብተዋል።
የሚሰጣቸውን የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እና በምርጫቸው ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን የሚያገለገሉ መኾኑን የሊቦ ከምከም ወረዳ ኮማንድፖስት አስታውቋል። የ51ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ሬጅመንት አዛዥ እና የሊቦ ከምከም ወረዳ እና የአዲስ ዘመን ከተማ ኮማንድፖስት አዛዥ ሻለቃ ጌታ በላይነህ ሠራዊቱም ኾነ ሕዝቡ ሰላም ይፈልጋል ነው ያሉት።
ሰው እንዲሞት አንፈልግም ችግሮችን በሽምግልና፣ በንግግር እና በመድረክ መፍታት እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት። በጋራ እና በትብብር ሀገርንም ክልልንም መታደግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ በመሳሪያ የሚፈታ ችግር አለመኖሩን ሁሉም ተረድቶ በሰላም ወደ መንግሥት እና ሕዝብ በመምጣታቸው መደሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የቀሩ ታጣቂ ኃይሎችም ከማያዋጣ ሽፍትነት ተመልሰው ወደነበሩበት የሰላም ኑሮ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
